ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ የነበረው የሰላም ንግግር እንደተራዘመ ተነገረ
በአፍሪካ ኅብረት አዘጋጅነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በመጪው ዕሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም. ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የሰላም ድርድር መራዘሙ ተነገረ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የታቀደው ንግግር በሎጂስቲክ ምክንያት ነው የዘገየው።
በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ከሚደረገው ጥረት ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ኅብረት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ውይይት አዘጋጅቶ ነበር።
ሁለቱም ወገኖች ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ግብዣ የተቀበሉት ሲሆን፣ ሁለት ዓመት ሊያስቆጥር የተቃረበውን ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት በተመለከተ የደቡብ አፍሪካው ድርድር ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛነት ሊካሄድ የታቀደ ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እነዚሁ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት የድርድሩ መራዘም ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ እና እስካሁንም አዲስ ቀን እንዳልተቆረጠ ጠቅሰዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራል መንግሥቱ፣ የትግራይ አመራሮችም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት የሰጡት አስተያየት የለም።
ይህንን በአፍሪካ ኅብረት የተዘጋጀውን የሰላም ንግግር የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የሚመራ ሲሆን፣ የኬንያው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ ንግኩካ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ረቡዕ ረፋድ የአፍሪካ ኅብረት ያቀረበውን የሰላም ድርድር ጥሪ ግብዣ ከመንግሥት የቀደመ አቋም ጋር የሚስማማ ነው በማለት ተቀብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የድርድር ጥሪውን የተቀበለው “ግጭቱን በሰላም ለማብቃት እና ካለቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ካለው አቋም ጋር የሚጣጣም” በመሆኑም እንደሆነ ጠቅሷል።
የትግራይ አመራሮች የአፍሪካ ኅብረትን ግብዣ ቢቀበሉትም ተጨማሪ ማብራሪያዎች እንዲሰጣቸው ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
በዚህ የሰላም ውይይት ላይ ተሳታፊዎች፣ ታዛቢዎች እና ዋስትና ሰጪዎች ተጋብዘው እንደሆነ እና የዓለም አቀፉ ማኅብረተሰብ ስለሚኖረው ሚና በተመለከተ ኅብረቱ ማብራሪያ ይሰጠን ብለዋል።
በተጨማሪም ትግራይ ለምትልከው ተደራዳሪ ቡድን፣ ጉዞ የደኅንነት ዝግጅቶችን እና ሎጂስቲክስን በተመለከተ ኅብረቱ ምን እንዳሰበም ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረት መስከረም 21/2015 ዓ.ም. የንግግር ግብዣ ደብዳቤ በአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ተፈርሞ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ነው የተላከው።
በዚህም የሰላም ንግግር ግብዣ ጥሪ መሠረት እሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ውስጥ ሊካሄድ በታቀደው “የሰላም ውይይት” ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል።
የአፍሪካ ኅብረት “በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ይህ የሰላም ውይይት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት መሠረት የሚሆኑ መርሆች፣ የአጀንዳ ጉዳዮች፣ አሰራሮች እና የጊዜ ሰሌዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል” ብሏል።
ንግግሩ እንደታቀደው በቀጣይ ቀናት ውስጥ የሚካሄድ ከሆነና ግጭቱን ማስቆም ከቻለ፣ ከዚህ ጦርነት አንጻር ለአፍሪካ ኅብረት ትልቅ ስኬት ይሆናል።
የአፍሪካ ኅብረት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ተፋላዊ ወገኖችን ወደ ንግግር ጠረጴዛ ለማምጣት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ ከረጅም ጊዜ ጥረት በኋላ የአሁኑ ሁለቱን ወገኖች ፊት ለፊት በማገናኘት የመጀመሪያው ስኬቱ ይሆናል።
ለአምስት ወራት የዘለቀው የተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ለማደራደር ይህ የአፍሪካ ኅብረት ጥሪ የመጀመሪያው ይፋዊ ሙከራ ነው።
ጋብ ብሎ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር እንደገና ማገርሸቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በአስከፊ ደረጃ መባባሱን የአውሮፓ ኅብረት ከሰሞኑ አስታውቋል።
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች 13 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እርዳታ ፈላጊ እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።