ከፍተኛው እራስን የማጥፋት ቁጥር በአፍሪካ እንደተመዘገበ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

በመላው ዓለም ከሚመዘገበው እራስን የማጥፋት ክስተት ከፍተኛ ቁጥር ያለው አፍሪካ አህጉር ውስጥ እንደሚፈጸም የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ።

እንደ ድርጅቱ መግለጫ ከሆነ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ከተመዘገበባቸው አስር አገራት ስድስቱ የሚገኙት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ነው።

በአህጉሪቱ የሥነ አእምሮ ህክም እና ድጋፍ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቁጥርም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጿል። በዚህም በአፍሪካ ውስጥ አንድ ሳይኪያትሪስት ሐኪም ለግማሽ ሚሊዮን ያህል ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል።

ይህ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው የባለሙያና የተጠቃሚዎች ምጥጥን አሃዝ በአንድ መቶ እጥፍ ያነሰ ነው።

በአፍሪካ ከሚኖሩ 100,000 ሰዎች ውስጥ 11 ሰዎች እራሳቸውን ያጠፋሉ ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በዓለም ላይ አማካይ ነው ተብሎ ከተቀመጠው ከ100,000 ሺህ ዘጠኝ ሰዎች እራሳቸውን የማጥፋት ክስተት አኳያ ከፍተኛው እንደሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት የጤና ተቋም ገልጿል።

ለሰዎች እራስን የማጥፋት ድርጊት እንደምክንያት በቀዳሚነት የተቀመጠው የአእምሮ ጤና ችግር ሲሆን፣ ይህም አስከ 11 በመቶ ለሚሆኑት ሰበብ እንደሆነ ተነግሯል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በአፍሪካ አህጉር ውስጥ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች በአብዛኛው የሚገኙት በከተሞች አካባቢ ስለሚሆን፣ በገጠሩ ክፍል ያሉ ነዋሪዎች አገለግሎቱን የማግኘት ዕድላቸውን ያጠበዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ክልል ዳይሬክተር የሆኑት ማስሂዲሶ ሞኤቲ እንደሚሉት፣ በአገራት የጤና ፕሮግራሞች ውስጥ የአእምሮ ጤና ችግሮችን የመከላከሉ አማራጭ ቅድሚያ ስለማይሰጠው እራስን የማጥፋት ሁኔታ ዋነኛ የኅብረተሰብ ጤና እክል ሆኗል።

እራስን የማጥፋትን ክስተቶች ለመከላከል ግንዛቤን ለመፍጠርና እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለማበረታታት የዓለም የጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ ውስጥ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እኣካሄደ ነው።

ይህ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ የተጀመረው በመጪው መስከረም 30 ከሚከበረው የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ቀደም ብሎ ነው።

በዚህም ዘመቻው የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ጋር መልዕክቱን ለማድረስ አቅዶ እየሰራ ነው።