ለማግባት የ‘ድንግልና ማስረጃ’ የምስክር ወረቀት የሚያስፈልጋቸው ኢራናውያን ሴቶች

ኢራን ውስጥ ጋብቻ ለመፈጸም ድንግል ሆኖ መገኘት ለሙሽሪቶችም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው እንደ ትልቅ ነገር ነው የሚታየው።

አንዳንድ ጊዜም ወንዶች የሚያገቧቸውን ሴቶች ድንግልና ለማረጋገጥ የምስክር ወረቀት እንዲያመጡ ይጠይቃሉ።

የድንግልና ማስረጃ የምስክር ወረቀት የዓለም ጤና ድርጅት ሰብዓዊ መብቶችን ይጻረራል በማለት የሚያወግዘው ተግባር ነው።

ተቋሙ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት ይህንን ልምድ በመቃወም በርካቶች ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

“ድንግል ስላልሆንሽ እንዳገባሽ አታለልሽኝ። ማንም እውነቱን ቢያውቅ አያገባሽም” ይህ የተነገራት ማሪያ የተባለች ግለሰብ ስትሆን፣ ከባሏ ጋርም ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ ከፈጸሙም በኋላ ነው።

ምንም እንኳን ደም ባይፈሳትም ከዚህ በፊት ግንኙነት ፈጽማ እንደማታውቅ ምላ ተገዝታ ብትነግረውም እርሱ ግን አላመናትም። የድንግልና ማስረጃ የምስክር ወረቀት እንድታመጣም ጠየቃት።

ይህ በኢራን ውስጥ የተለመደ ነው። በርካታ ጥንዶች ከተጫጩ በኋላ በርካታ ሴቶች የህክምና ባለሙያ ጋር ሄደው ወሲብ ፈጽመው እንደማያውቁ የሚያሳይ ምርመራ ያከናውናሉ።

ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው የድንግልና ምርመራ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ድጋፍ የለውም።

የማሪያ ሰርቲፊኬት እንደሚያሳየው የድንግልናዋ (ሃይመን) ዓይነት “ተለጣጭ” ሲሆን ይህም ማለት ከወሲብ በኋላ ደም ላይፈስ ይችላል ማለት ነው።

“ህሊናዬን በጣም ነው የነካኝ። ምንም ስህተት አልሰራሁም ነገር ግን ባለቤቴ ሲወጣና ሲገባ ይሰድበኝ ጀመር። ልቆጣጠረው ስላልቻልኩም የተወሰኑ ክኒኖች ወስጄ ራሴን ለማጥፋት ሞከርኩ” ትላለች።

ነገር ግድ ዕድለኛ ሆና በጊዜው ሆስፒታል በመወሰዷ ሕይወቷ ተረፈ።

“እነዚያን የጨለማ ቀናት መቼም አልረሳቸውም። በዚያን ጊዜ 20 ኪሎ ግራም ቀነስኩ” በማለት ትናገራለች።

ልምዱን ለማቆም እየተደረጉ ያሉ ዘመቻዎች

የማሪያ ታሪክ የበርካታ ኢራናውያን ሴቶች እውነታ ነው። ከጋብቻ በፊት ድንግል መሆን ለበርካታ ሴቶች እና ቤተሰቦቻቸው አሁንም ቢሆን ወሳኝ ተደርጎ ነው የሚታየው። በዚህ የባህል ወግ አጥባቂነት ስር የሰደደ ዕሴት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች መለወጥ ጀምረዋል። በአገሪቱ ያሉ ሴቶች እና ወንዶች የድንግልና ምርመራን ለማስቆም ዘመቻ እያደረጉ ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር በበይነ መረብ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ወደ 25 ሺህ የሚጠጉ የተቃውሞ ፊርማዎችን ማሰባሰብ ተችሏል።

በኢራን ውስጥ የድንግልና ምርመራ በበርካታ ኢራናውያን ዘንድ በይፋ ተቃውሞ ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው ነው።

“ይህ የግል መብትን የሚጥስ ነው። በጣም የሚያዋርድና የሚያሳፍር ተግባር ነው” ትላለች ኔዳ።

ኔዳ በዋና ከተማዋ ቴህራን የ17 ዓመት ታዳጊና ተማሪ እያለች ነው ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ወሲብ የፈጸመችው።

“ደነገጥኩ፣ ቤተሰቦቼ ቢያውቁ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ፈራሁ” በማለት በወቅቱ የተሰማትን ትናገራለች።

ስለዚህ ኔዳ በወቅቱ ከተሰማት እፍረት ለመውጣትም ድንግልናዋን (ሃይመኗን) በጥገና ለመመለስ ወሰነች።

ምንም እንኳን ይህ ጥገና ሕገ ወጥ ባይሆንም አደገኛ ማኅበራዊ አንድምታዎች ስላሉት የትኛውም ሆስፒታል ይህንን ቀዶ ህክምና ለማድረግ አይስማማም።

እናም ኔዳ በከፍተኛ ገንዘብ በድብቅ የሚሰራ የግል ክሊኒክ አገኘች።

“ያጠራቀምኩትን በሙሉ ለዚህ ቀዶ ህክምና አወጣሁ። ላፕቶፕን፣ ሞባይል ስልኬን እና የወርቅ ጌጣጌጠን ሸጥኩ” ትላለች።

ከገንዘቡ በተጨማሪ የሆነ ችግር ቢፈጠር ሙሉ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ሰነድ መፈረም ነበረባት።

ከዚያም 40 ደቂቃ ያህል የፈጀ የቀዶ ህክምና ተደረገላት።

ለማገገምም በርካታ ሳምንታት አስፈልገዋታል።

“በከፍተኛ ህመም ላይ ነበርኩ። እግሮቼን ማንቀሳቀስ አልቻልኩም” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

ሁሉንም ነገርም ከወላጆቿ ደብቃ ነበር።

“በጣም ብቸኝነት ተሰምቶኝ ነበር። ነገር ግን እነሱ ያውቁ ይሆን የሚለው ፍርሃት ህመሙን እንድቋቋም የረዳኝ ይመስለኛል” በማለት ታስረዳለች።

ሆኖም ገንዘቧን ሁሉ ያፈሰሰችበትና ከባድ ህመም የተቋቋመችበት ይህ ሂደት ከንቱ ነበር።

ከአንድ ዓመት በኋላ ሊያገባት የሚፈልግ ሰው ተዋወቀች። ወሲብ ሲፈጽሙ ግን ደም አልፈሰሳትም እናም የተባለው ቀዶ ህክምና አልተሳካም ነበር።

“ይህ ፍቅረኛዬ ለጋብቻ ልታታልለኝ ሞከረች ብሎ ከሰሰኝ። በዚያም አላበቃም ‘ውሸታም ነች’ ብሎ ጥሎኝ ሄደ” ብላለች።

ከቤተሰብ የሚመጣ ጫና

የዓለም ጤና ድርጅት የድንግልና ምርመራ ሥነ ምግባር የጎደለው እና ሳይንሳዊ ድጋፍ የሌለው እንደሆነ ገልጾ፣ በተደጋጋሚ ቢያወግዝም፤ ድርጊቱ አሁንም በበርካታ አገራት ውስጥ ለምሳሌም ያህል በኢንዶኔዥያ፣ በኢራቅ እና በቱርክ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢራን የህክምና ተቋት የድንግልና ምርመራን የሚያከናውኑት የፍርድ ቤት እና የመድፈር ክሶች በመሳሰሉ ልዩ ሁኔታዎች ምክንያት ብቻ ነው።

ነገር ግን አብዛኛው የድንግልና ማረጋገጫ ጥያቄ የሚመጣው ለመጋባት ካሰቡ ጥንዶች ነው። በርካታ ሴቶችም ለምርመራው ከእናቶቻቸው ጋር ሆነው ወደ ግል ክሊኒኮች ያቀናሉ።

የማህፀን ሐኪሞች ወይም አዋላጆች ምርመራ ካካሄዱ በኋላ የምስክር ወረቀት ይሰጣሉ። የምስክር ወረቀቱ ምርመራ የተደረገላት ሴት ስም፣ የአባቷን ስም፣ የብሔራዊ መታወቂያዋ ቁጥር አንዳንዴም ፎቶን የያዘ ነው።

በተጨማሪም የድንግልናዋን (የሃይመኗን) ሁኔታ በማብራራትና “ይህች ልጅ ድንግል ትመስላለች” የሚል ዓረፍተ ነገርንም ያካተተ ነው።

ብዙ ወግ አጥባቂ በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ሰነዱ በሁለት ምስክሮች ይፈረማል። በተለምዶም የእናቶች ፊርማ ምስክር ወረቀቱ ላይ ያርፋል።

ዶክተር ፋሪባ ለዓመታት የድንግልና ማስረጃ የምስክር ወረቀት ሲሰጡ ቆይተዋል። የህክምና ባለሙያዋ በጣም የሚያሳፍርና የሚያዋርድ ተግባር መሆኑን ቢቀበሉም፣ ነገር ግን ብዙ ሴቶችን እየረዱ እንደሆነ ያምናሉ።

“በርካታ ሴቶች በቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ይገኛል። አንዳንድ ጊዜ ጥንዶቹን በቃላት እዋሻቸዋለሁ። ጥንዶቹ ወሲብ ከፈጸሙ እና መጋባት ከፈለጉ ሴቷ ድንግል መሆኗን በቤተሰቦቻቸው ፊት እናገራለሁ” ይላሉ።

ለብዙ ወንዶች ድንግል ማግባት አሁንም ቢሆን መሠረታዊ ነገር ነው።

“ሴት ልጅ ከማግባቷ በፊት ድንግልናዋን ካጣች እምነት ሊጣልባት አይችልም፤ ባሏን ትታ ወደ ሌላ ወንድ ትሄዳለች” ሲል የሺራዝ ነዋሪ የሆነው የ34 ዓመቱ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ አሊ ተናግሯል።

ነገር ግን እሱ በበኩሉ ከ10 ሴቶች ጋር ወሲብ እንደፈፀመ ይናገራል።

አሊ በኢራን ማኅበረሰብ ውስጥ ለሴቶች እና ለወንዶች የተለያዩ መስፈርቶች እንደተቀመጡ ይቀበላል፤ ነገር ግን ከማኅበረሰቡ ባህልና ወግ ለመውጣት ምንም ምክንያት አይታየኝም ብሏል።

“ማኅበራዊ ደንቦች፣ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ነፃነት እንዳላቸው ይደነግጋሉ” በማለትም ምክንያቱን ያስረዳል።

የአሊን አመለካከት በርካቶች በተለይም ወግ አጥባቂ በሆኑ ገጠራማ የኢራን አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚጋሩት ነው።

ምንም እንኳን በድንግልና ምርመራ ላይ ተቃውሞዎች እየጨመሩ ቢሄዱም፣ ይህ አስተሳሰብ በኢራን ባህል ውስጥ በጣም ሥር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙዎች በመንግሥት እና በሕግ አውጪዎች ላይ አጠቃላይ ድርጊቱን ማገድ በቅርቡ የማይቻል ነው ብለው ያምናሉ። 

የወደፊቱ ተስፋ

ማሪያ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ ካደረገች ከአራት ዓመት በኋላ ጥቃት ከሚያደርስባት ባሏ ጋር በመጨረሻ በፍርድ ቤት መፋታት ችላለች።

“ወንድን እንደገና ማመን በጣም ከባድ ይሆናል። በቅርብ ጊዜ የማገባም አይመስለኝም” በማለት ትናገራለች።

በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ማሪያ የድንግልና የምስክር ወረቀትን በመቃወም ፊርማቸውን የበይነ መረብ ላይ ካኖሩ ኢራናውያን መካከል አንዷ ሆናለች።

ምንም እንኳን በቅርቡ ለውጥ ይመጣል ብላ ባትጠብቅም፣ ምናልባትም በሕይወት ዘመኗ ውስጥም ባይሆን፣ አንድ ቀን ሴቶች በአገሯ ውስጥ የበለጠ እኩልነት እንደሚያገኙ ታምናለች።

“አንድ ቀን ለውጡ እውን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። ወደፊት ሴት ልጆች እኔ ባለፍኩበት የሕይወት መስመር እንደማያልፉ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች።

* በዚህ ታሪክ ውስጥ የተካተቱት ሴቶች ማንነታቸውን ለመጠበቅ የሁሉም ስም ተቀይሯል።