ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ባሎቻቸውን ገድለዋል የተባሉ ሦስት ሴቶች በአንድ ቀን በሞት ተቀጡ
የኢራን ባለሥልጣናት ባሎቻቸውን በመግደል የተወነጀሉ ሦስት ሴቶችን ረቡዕ ዕለት በሞት መቅጣታቸውን የሰብዓዊ መብት በጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ።
የኢራን የሰብዓዊ መብት ቡድን እንደገለጸው ሦስቱ ሴቶች ባለፈው ሳምንት ብቻ ከተገደሉት 32 ሰዎች መካከል ናቸው።
ከተገደሉት መካከል ያለዕድሜዋ በ15 ዓመቷ ያገባችውን ባል በመግደል ወንጀል የተፈረደባት ሴትም ትገኝበታለች።
ባለሥልጣናቱ የሞት ቅጣትን በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክረዋል ቀጥለዋል ተብሎ ይታመናል። በዚህም ካለፈው ዓመት በእጥፍ የሚበልጡ ሰዎችን ገድለዋል።
የመብት ተሟጋቾች እንደዘገቡት ኢራን ከየትኛውም አገር በበለጠ ብዙ ሴቶችን ትገድላለች። ከእነዚህም መካከል አብዛኛዎቹ ባሎቻቸውን በመግደል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል ተብሎ ይታሰባል።
የኢራን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው ያለዕድሜዋ ያገባችው ሶሄይላ አባዲ እስር ቤት ውስጥ ነው በስቅላት የተቀጣችው።
ሶሄይላ ከ10 ዓመት በፊት በ15 ዓመቷ ያገባች ሲሆን ባሏን ገድላለች በሚል ነው ፍርዱ የተላለፈባት።
የቅጣት ውሳኔን ያስተላለፈው ፍርድ ቤት ግድያው የተፈጸመበትን ምክንያት “የቤተሰብ አለመግባባት ነው” ሲል አሳውቋል።
ረቡዕ ዕለት የተገደሉ ሌሎች ሁለት ሴቶችም በተመሳሳይ ባሎቻቸውን በመግደል ወንጀል ተከሰው ቅጣት ተፈርዶባቸዋል ሲል ቡድኑ ገልጿል።
አንቂዎች እንደሚሉት ብዙዎቹ ምክንያቶች የቤት ውስጥ አለመግባባትን ቢያካትትም የኢራን ፍርድ ቤቶች ይህንን ግምት ውስጥ አያስገቡም።
የኢራን ባለሥልጣናት የተፈጸሙትን የሞት ፍርድ ውሳኔዎች በይፋ ስለማያሳውቁ ትክክለኛውን አሃዝ አይገኝም።
በሚያዝያ ወር በሁለት የመብት ተሟጋች ቡድኖች የታተመ ጥናት እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ኢራን ውስጥ ከተፈጸሙት የሞት ፍርዶች 16.5 በመቶዎቹ ብቻ ይፋ ሆነዋል።
በዚህ ዓመት የወጡ መረጃዎች ደግሞ የሞት ቅጣት ቁጥሩ ከፍ ማለቱን ገጸዋል።
ኢራንን በቅርብ ወራት ውስጥ “አሰቃቂ” የሞት ቅጣት ፈፅማለች በማለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚህ ሳምንት ከሷል።
በ2022 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከ250 በላይ ሰዎችን ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ይበልጣል።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዲያና ኤልታሃዊ "የመንግሥት አካላት በመላ አገሪቱ በሕይወት የመኖር መብት ላይ አስጸያፊ ግድያዎችን እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
ጥፋተኛ ተብለው ከተፈረደባቸው መካከል የተወሰኑት በጅምላ በሞት እንዲቀጡ መደረጉን የመብት ቡድኑ ዘግቧል።
ሰኔ 6 ከአንድ እስር ቤት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል። ሰኔ 15 በሌላ እስር ቤት በተመሳሳይ በደርዘን የሚቀጠሩ ግለሰቦች የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል።
በዚህ ቁጥር ውስጥ የአናሳ ጎሳ አባላት ትልቁ ድርሻ አላቸው።
የባልቺ ጎሳ አባላት ከኢራን አጠቃላይ ሕዝብ 5 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይይዛሉ። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሚታመነው እና በዚህ ዓመት ተገድለዋል ተብለው ከሚገመቱት አራት ሰዎች ከአንድ በላይ የሚሆኑት የዚህ ብሔረሰብ አባላት ናቸው።