“ፀሐፊነቴን ከዩኒቨርስቲ በኋላ ያረጋገጡልኝ የፌስቡክ ጓደኞቼ ናቸው”ደራሲ ኤልሳ ሙሉጌታ

ደራሲ ኤልሳ ሙሉጌታ የአዳም ረታ አድናቂ ነኝ ትላለች። ማድነቅ ብቻ ሳይሆን 15 አጫጭር ልቦለዶችን በያዘው 'ሐምራዊ ተረኮች' መጽሐፏ ላይ የእርሱን የአጻጻፍ ስልት መሞከሯን ትናገራለች።

ኤልሳ 15 ተረኮቿ ውስጥ ወዲያ ወዲህ በማለት ኑሯቸውን የመሠረቱትን ገጸ ባህሪያት ከእውኑ ዓለም፣ ከሦስት የተለያዩ አካባቢዎች ጨልፋ መውሰዷንም አልሸሸገችም።

እነዚህ ገጸ ባህሪያት በአንድ ወቅት እርሷ ባደገችባቸው አካባቢዎች የኖሩ ናቸው። አሁን ግን በሐምራዊ ተረኮች ገጾች ውስጥ እንዲኖሩ የፈለገችው ጫጫ ነው።

ለዚህ ደግሞ ጫጫ ከትውልድ ትውልድ ሲነገር የመጣው ንግርት ሰበበ ምክንያት ሆኗል።

ቢቢሲ ከኤልሳ ሙሉጌታ ጋር ስለ ሥራዋ አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

* * * *

ቢቢሲ- የመጽሐፍሽ ርዕስ 'ሐምራዊ ተረኮች' ይሰኛል። በታሪኮቹ ውስጥም ሆነ በሽፋን ሥዕሉ ላይ ግን ሐምራዊነትን አላየሁም። ለምንድ ነው ርዕሱን ሐምራዊ ተረኮች ያልሽው?

ኤልሳ- ብዙ ሰው ነው የሚጠይቀኝ፤ ሐምራዊ ነገር የለውም፤ ሽፋኑ ጥቁር እና ነጭ ነው። እውነት ነው የለውም። ርዕሱን ካወጣሁ በኋላ በታሪኮቹ ውስጥ ሐምራዊ ቀለም የሚመስሉ የሆነ 'ፓተርን' ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ።

ምንድን ነው ግን. . . ሰዎች ሁልጊዜ ለራሳቸው ብቻ የሚሰጡት ትርጉም አላቸው መሰለኝ። እኔ መጽሐፌን ሐምራዊ ስል የተገመዱ ታሪኮች ናቸው የታዩኝ። ልክ ላይሆን ይችላል። ግን የተለያዩ ታሪኮች ሆነው ሕብር የሠሩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው።

ቢቢሲ- በአጭር ልቦለዶችሽ ውስጥ የተሳሉት ገጸ ባህሪያትን ስመለከት ሁሉም ማለት በሚያስደፍር መልኩ በዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ያሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተገፉ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። ነገር ግን አያማርሩም፤ እንዲያው ቀና እና አመስጋኝ ናቸው። ሆን ብለሽ ነው ሁሉንም እንደዚያ ያደረግሻቸው? የሚኖሩበት የልቦለድ ዓለም እውነት ክፋት የለበትም?

ኤልሳ- [ሳቅ] አላት፤ ዓለም በጣም ክፉ ነች። ክፉ ጎንም አላት። ብዙ ጊዜም ለሰዎቿ የምታሳየው ያንን ክፉ ገጿን ነው። ለአብዛኞቻችን እንደዚያ ናት። በመጽሐፌ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ገጸ ባህሪያት፤ ተረት የሚመስሉ ፋንታሲዎች ጨመርኩባቸው እንጂ በገሃዱ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ልጅ ሆኜ ከማቃቸው ሰዎች ተነስቼ ነው ታሪኩን የጻፍኩት።

ለምሳሌ መንደሪን የምትሸጠው ዐይነ ስውር ሴትዮ ታሪክ፣ የመጀመሪያ ደረጃ በተማርኩበት ትምህርት ቤት አካባቢ መንደሪን የምትሸጥ ዐይነ ስውር ሴት ነበረች። ግን ከእርሷ የማስታውሰው ይህንን ብቻ ነው። ሌላው ታሪክ ግን ፈጠራ፣ ተረት ነው፤ የእኔ ሙሉ ፈጠራ ያለበት።

እንዳልከው ገጸ ባህሪያቱ ደሃዎች ናቸው። አብዛኞቹ እኔ ባደግኩበት አካባቢ እና በዚያ ዘመን ዝቅተኛ ኑሮ የሚመሩ ሰዎች አያማርሩም። ያለውን ሕይወት ተቀብሎ የሚኖር ማኅበረሰብ ነበር። ማማረር የምንኖረውን ሕይወትን ካለመቀበል የሚጀምር ይመስለኛል። ያ ያደግኩበት ማኅበረሰብ ግን ዕጣ ፈንታውን ተቀብሎታል። ጥሩ በማድረግ የሚያምን ማኅበረሰብ ነው። በእርግጥ የሚቆጠር ሀብት የላቸውም። አለመኖሩን ግን በማማረር አይገልጸውም። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ ዛሬም ድረስ አሉ።

ቢቢሲ- መጀመሪያ ላይ በጽሑፍ የምትታወቂው ፌስቡክ ላይ ነበረ። ፌስቡክ ላይ ለረዥም ጊዜ ስትጽፊ ቆይተሻል። መቼ ነው አሁን ደግሞ መጽሐፍ ማሳተም አለብኝ ያልሽው?

ኤልሳ- እነዚህን ታሪኮች ፌስቡክ ላይ ጽፌያቸው አላውቅም። ልጅ ሆኜ የማውቃቸው የሆኑ ሰዎች ነበሩ። ካደግኩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ቶሎ ወደ ማኅበረሰቡ አልተቀላቀልኩም። ተከራይ ስለሆንኩ እና በየጊዜው ሰፈር ስለምቀያይር ሁሌ ባይተዋር ነው የምሆነው። በተለይ ተከራይ ሲኮን ይህ በደንብ ይስተዋላል።

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልቅ ከተሞች ቀስ እየተባለ ነው ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል የሚመጣው። እኔ እንዳደግኩበት አካባቢ ሁሉም በጋራ አይኖርም፤ አዲስ አበባ መኖር ስጀምር የኖርኩበት አካባቢ ማኅበራዊነት ይናፍቀኝ ጀመር። አዲስ አበባ ሆኜ ልክ ባሕር ማዶ እንዳለ ሰው [ሳቅ] ማኅበራዊ ሕይወቱ ይናፍቀኝ ነበር። የማውቃቸው ሰዎች፣ ባህሪያቸው ይናፍቀኝ ነበር። ያኔ ነው የተለዩ ናቸው ያልኳቸውን ሰዎች ዝም ብዬ መተረክ የጀመርኩት።

. . . የልምድ አዋላጇ እትዬ አሰገድ፣ እህቶቼን ያዋለዱት ሴት ናቸው፤ . . . ቤተሰቦቼ መምህራን ስለነበሩ የሚመደቡበት አካባቢ በሙሉ መብራት የሌለው፣ ከከተማ የራቀ በመሆኑ በገጸ ባህሪያት የሳልኳቸው ሰዎችን ሁሉ የማግኘት፣ የማስተዋል ዕድል አግኝቻለሁ።

መጽሐፍ ይሆናል ብዬ ሳይሆን ደስ ስለሚለኝ፣ ወደ ልጅነቴ ስለሚመስለኝ ብቻ ያንን እየጻፍኩ አስቀምጥ ነበር። አንድ ጓደኛዬ የጻፍኩትን ካየ በኋላ ዓላማዬ ምንድን እንደሆነ ጠየቀኝ። ያኔ ግራ ገባኝ። ለእኔ ጽፌ ማስቀመጡ ነበር ደስታ የሚሰጠኝ። ከዚያ በኋለ ካደግኩባቸው ትንንሽ ከተሞች አንዱ በሆነው ጫጫ የሚነገር ንግርት፣ ስለማጂክ ሪያሊዝም ካወቅሁ በኋላ፣ ጨማምሬ መጽሐፍ እንዲሆን አደረግኩ ማለት ነው።

ቢቢሲ- አሁን ከመልስሽም ስረዳ፣ በሥራዎችሽም ውስጥ እንደሚስተዋለው ታሪኮቹ በልጅነት ትውስታዎችሽ ውስጥ የታጨቁ ናቸው።

ኤልሳ- አዎ ልጅነቴ ነው። ልጅነቴን እንደዚሁ እወደዋለሁ መሰለኝ። ብዙ ጊዜም ቢሆነው የሚርቀኝ አይመስለኝም። ለምሳሌ የቆዩ ነገሮችን አስታውሳለሁ። . . .ጭንቅላቴ ውስጥ የድሮ ነገሮች አሉ። ከአራት ዓመቴ ጀምሮ የማውቃቸው ነገሮች በሙሉ አእምሮዬ ውስጥ አሉ። ግን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ነገሮችን እረሳለሁ። አሁን ለምሳሌ [ለቃለ ምልልስ] እንደተቀጣጠርን ረስቼው ነበር [ሳቅ]. . . እና ልጅነቴ ላይ በጣም ሙጭጭ ብዬ ነው የቀረሁት።

ደግሞ በጣም ደስ የሚል ልጅነት ነበረኝ። ነጻነት ነበረኝ። የፈለግኩትን እንዳደርግ የሚተው ቤተሰብ ነበረኝ። በጣም ነበር እየዞርኩ አካባቢዬን የምቃኘው። በዚህም የተነሳ ብዙ ነገሮችን ማስተዋል ችያለሁ። በዚህም የተነሳ ልጅነቴን እወደዋለሁ።

ቢቢሲ - እንደነገርሽኝ የተለያዩ አካባቢዎች ኖረሻል። ነገር ግን ገጸ ባህሪያቶችሽ በሙሉ የሚኖሩት ጫጫ ነው። ጫጫን ከኖርሽባቸው ሌሎች ስፍራዎች ሁሉ ለምን መረጥሻት?

ኤልሳ - ቤተሰቦቼ ከሌላ አካባቢ ተቀይረው ጫጫ ስንመጣ አስራ አንድ ዓመት አካባቢ ይሆነኛል። እና ነፍስ ያወቅኩት እዚያ ነው ማለት እችላለሁ። ብዙ ትዝታ ደግሞ የሚኖረው ደግሞ ሲጎረመስ፣ ነፍስ ሲታወቅ ነው። ለልቤም ቅርብ የሆነው እድሜም ስለሆነ ይመስለኛል።

ለተማዋ ግን ከኖርኩባቸው ሌሎች ስፍራዎች ሁሉ በተሻለ የተለየ ስፍራ አለኝ። በተጨማሪም በመጽሐፌ ውስጥ የተጠቀምኩት ንግርት ያለው እዚያ ጫጫ ውስጥ ስለሆነ ገጸ ባህሪዎቼን በሙሉ እዚያ ማድረግ ነበረብኝ። ከዚያ በተጨማሪ አሁን ስሟ ስለተቀየረ ስሟን በቋሚነት ማኖር ፈለግኩኝ።

ቢቢሲ- እኔ መጽሐፉን ሳነበው እንደ አጭር ልቦለድ አልነበረም ያየሁት። ጫጫ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ ሌላ የሚያስተሳስራቸውም ድርም አለ። ሆን ብለሽ ያንን ለማድረግ የተከተልሽው ስልት አለ?

ኤልሳ- መጽሐፌ ውስጥ የምታገኛቸው ገጸ ባህሪያት የሦስት አካባቢ ሰዎች ናቸው። ጊናገር የሚባል አንድ አካባቢ አለ። እኛ እዚያ በምንኖርበት ወቅት ቦታው መብራት አልነበረውም። ከዚያ ጫጫ አለ፤ በመቀጠል ደግሞ ደብረ ብርሃን የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እነዚህን ሰዎች ነው ሰብስቤ በመጽሐፌ ውስጥ ጫጫ እንዲኖሩ ያደረግኳቸው። መጽሐፌ ውስጥ በትክክል የጫጫ ሰዎች ያሉት ሦስት ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ከሌላ አካባቢ ያመጣኋቸው ናቸው።

መጽሐፌ ወደ ህትመት ከመሄዱ በፊት ያሳየሁት ልጅ ዓላማሽ ምንድን ነው ሲለኝ፣ እነዚህ ገጸ ባህሪያት የብቻ ታሪክ ከሚኖራቸው የሆነ የሚገናኙበት መንገድ ቢኖር በማለት በሆኑ በሆኑ ታሪኮች ላገናኛቸው ሞክሬያለሁ። አዳም ረታንም በጣም ነው የምወደው እና በሥራዎቼ ውስጥ የአዳምን ሕጽናዊነትም ለመሞከር ጥረት አድርጌያለሁ።

ቢቢሲ- ሴት ደራሲ በመሆንሽ በተለይ ለእኔ በጣም ቅርብ ታሪክ፣ ገጸ ባህሪ ነው የምትይው አለ እዚህ መጽሐፍሽ ውስጥ?

ኤልሳ- እንዳልኩት መጽሐፌ ውስጥ የማውቃቸውን ሰዎች ነው በገጸ ባህሪነት የሳልኩት። እና ሳላስባቸው 13 ሰዎች በታሪኩ ውስጥ ተካትተዋል። ግን ያ የሆነው ለሴቶች ለማድላት ፈልጌ. . .ከሴትነቴ አንጻር ሳይሆን ሳላስበው ውስጤ ያለውን ነገር ዝም ብዬ ሳሰፍረው ነው በዚያ መልክ የሆነው። በተለይ ግን እናቶች ለገጸ ባህሪ ምርጫ እወዳለሁ። . . . . ግን እውነቱን ለመናገር ገለልተኛ ሆኜ ለመጻፍ ነው የሞከርኩት። ግን ሳላውቀው ሴት ስለሆንኩ፣ ብዙ ነገርንም የማውቀው በሴቶች መነጽር በመሆኑ መጽሐፌ ላይ ሴት ገጸ ባህሪያት በዝተው ታይተዋል።

ቢቢሲ- ለመጀመርያ ጊዜ ጽሑፍ መክሊቴ ነው፣ የደራሲ ዕጣ ፈንታ አለኝ፣ ያልሽበትን ጊዜ ታስታውሸዋለሽ?

ኤልሳ - ልጅ ሆኜ ምን እንደምሆን አላውቅም ነበር። ምንድን ነው መሆን የምትፈልግው ተብዬ ስጠየቅ ምን እንደምሆን አላውቅም ነበር። [ሳቅ] ግን የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪ ብሆን ደስ ይለኝ ነበር። መጻፍ የጀመርኩት ጎንደር ዩኒቨርስቲ ለትምህርት ስሄድ ነው። ገና ልጅም ስለነበርኩ፣ ብቻዬንም ስለሆንኩ፣ ያኔ ነገሮችን ማስተዋል እና በተለየ መንገድ መግለጽ ጀመርኩኝ። ብዙ ሰዎችም የምጽፈውን ይወዱት ጀመር። ያኔ ግጥምም እጽፍ ነበር ፌስቡክ ላይ። ፌስ ቡክ ለእኔ ጥሩ ቦታ ነበር። ሰዎች ያዩልኝ እና አይዞሽ በርቺ ጎበዝ ሲሉኝ እየበረታሁ መጣሁ። ፀሀፊ ነሽ ሲሉኝ እኔም አላሳፈርኳቸውም እሺ አልኳቸው [ሳቅ]. . .

ቢቢሲ- ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ቆይታሽ በኋላ ያንቺን ፀሐፊነት ያረጋጋጡት የፌስቡክ ጓደኞችሽ ናቸው ማለት ነዋ።

ኤልሳ- አዎ!

ቢቢሲ- ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አባትሽ መጽሐፍሽን ካነበቡ በኋላ የጻፉልሽን ደብዳቤ አጋርተሽ ነበር። አባትሽ ደራሲ በመሆንሽ ኮርተዋል።

ኤልሳ - አዎ፤ በጣም ደስ አለኝ ሲኮራ፤ ደስ አለው። ከአባታችን ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ታላቅ ወንድም ነው። እና በእኔ እንደዚህ ኩ. . ር. . ት ሲል አይቸው አላውቅም እና በጣም ደስ አለኝ። [ሳቅ]. . . ብዙ ሰዎች እንብበውት እንደወደዱት ነግረውኛል፤ ቢያንስ ለእኔ የነገሩት እንደወደዱት ነው። እርሱን ሲነግሩኝም ደስ ብሎኝ ነበር። ከዚያ ደግሞ አባዬ ሲኮራ ስሜቴ የተለየ ነው።

ቢቢሲ- የዚህ ምናብ ባለቤት ያደረገኝ ገጠር መወለዴ ነው ትያለሽ?

ኤልሳ- እንደዚያ ሳይሆን፤ ተረትን መውደዴ ይመስለኛል ምናቤ በዚህ መልክ የሆነው። የማይሆኑ ነገሮችን እንደሚሆኑ ማሰብ እወድ ነበር። መጽሐፌን መጀመሪያ ያነበቡ ሰዎችም ተረት ይመስላል ብለውኝ ያውቃሉ። ነጻ መሆኔ፣ አስተዳደጌም ነው የዚህ ምናብ ባለቤት ያደረገኝ። እቃቃ ልጅ ሆኜ ስጫወት በራሴ ሕግ አይደል የምጫወተው? ለዚያም ይመስለኛል። በዋናነት ገጠር ማደጌ አይመስለኝም።