ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ
የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በየትኛውም ስፍራ፣ በማንኛውም ጊዜ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ ነው ተባለ።
ይህን ያሉት የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው በትዊተር ገጻቸው ላይ እርሳቸው እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኞች እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደሮች ጋር ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም. መገናኘታቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከፍትሕ ሚንስትሩ ጋር በመሆን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ስለሚደረገው ንግግር የፌደራል መንግሥትን አቋም በተመለከተ ለምዕራባውያኑ ተወካዮች ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በማብራሪያቸው ላይ የፌደራሉ መንግሥት፤ በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸናል ብለዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጨምረውም፤ የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ንግግር ያለ አንዳች ቅድም ሁኔታ እንዲጀመር ፍላጎቱ መሆኑን ለምዕራባውያኑ መናገራቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፈረዋል።
በህወሓት በኩል የሚደረገውን ድርድር በተመለከተ አወዛጋቢውን የምዕራብ ትግራይ ጉዳይን ጨምሮ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ባሉት ላይ የትግራይ ኃይሎች ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ከቀናት በፊት የህወሓት ሊቀመንበር ምንም አይነት ድርድር ከመጀመሩ በፊት የተቋረጡት መሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመር አለባቸው ማለታቸው ተዘግቧል።
የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ንግግር መምራት ያለበት የአፍሪካ ኅብረት እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት 20 ወራት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የቆዩት የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ስለሚደረገው ንግግር አቋማቸውን ባሳወቁበት ወቅት፣ ድርድሩ በበላይነት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲመሩ ጠይቀው ነበር።
በተጨማሪም የአምባሳደሮቹ እና የልዩ መልዕክተኞቹ ቡድን ወደ መቀለ እንዲጓዝ መንግሥት መፍቀዱንም አምባሳደር ሬድዋን አመልክተዋል።
አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን አስተዳደራቸው ከዚህ መርማሪ ኮሚሽን ጋር በትብብር መስራቱን እና ልዩነቶችን ለማጥበብ የተሰሩ ሥራዎችን ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ሕብረት እና ለምዕራብ አገራት ዲፕሎማቶች አብራርተናል ብለዋል።
በተያያዘም ከቀናት በፊት ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት ኮሚሽን ውይይት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገኛል።
የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችን የያዘው ኮሚሽን ከሐምሌ 18/2014 ዓ. ም. እስከ ሐምሌ 24/2014 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ያካሂዳል።
የድርድር ፍላጎት
ሁለት ዓመት ሊሆነው የተቃረበውን ጦርነት ለማብቃት በመንግሥትም ሆነ በህወሓት በኩል ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለ ሁለቱም ወገኖች አሳውቀዋል።
“ከህወሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው፤ የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦርነት እንደማያተርፍና ከሁለቱም ጎን የሚያለማ ወጣት እየረገፈና አገሪቱም የምታወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተናገሩት፣ መንግሥታቸው ከየትኛውም ወገን ጋር ሰላም ማውረድ እንደሚፈልግ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰባት አባላት ያለው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ጋር በኬንያ መንግሥት አሸማጋይነት በሚካሄድ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከአንድ ሳምንት በፊት የትግራይ ኃይሎችን የሚወክል በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ የሚገኙ አባላት ያሉት ልዑክ መዘጋጀቱንና ለድርድር ለመላክ ዝግጁ እንደሆኑ አሳውቀዋል።
የትግራይ አመራሮች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውንም በተመለከተ በደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በተጻፈው ደብዳቤ “ለሰላም ተጨማሪ ርቀት ለመሄድ ዝግጁ መሆናችን ከደካማነት ወይም ከስግብግብነት በመነጨ የቆምንለትን መርኅ ለመተው እንደ መዘጋጀት ተደርጎ መታየት የለበትም” ብሏል።
በዚህ ድርድርም በኬንያ መንግሥት መሪነት የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።
በመንግሥት እና በህወሓት በኩል ድርድር የማድረግ ፍላጎት እንዳለ በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ ሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎችን ከመሰየም ባለፈ ምንም አይነት ተግባራዊ የተጀመረ ነገር ስለመኖሩ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።