የጃፓን አየር መንገድ የመጀመሪያዋ ሴት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት የቀድሞዋ የበረራ አስተናጋጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሚትሱኮ ቶቶሪ የጃፓን አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር።
የሥራ ሕይወታቸውን የበረራ አስተናጋጅ ሆነው የጀመሩት ቶቶሪ ሹመት ሴት አመራሮች የሌሏቸውን በመላ አገሪቷ ያሉ ትላልቅ ኩባንያዎችን አሸማቆ ነበር።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃንም ይህንን ክስተት “የመጀመሪያዋ ሴት”፣ “የመጀመሪያዋ የቀድሞ የበረራ አስተናጋጅ” በሚሉ አርዕስተ ዜናዎች ነበር ይዘውት የወጡት።
የ59 ዓመቷ ቶቶሪ አየር መንገዱ ከሚሾማቸው የንግድ ሊሂቃን መካከል የወጡ አይደሉም።
ከዚህ ቀደም በዚህ ኃላፊነት ላይ ከተሾሙት አስር ወንዶች መካከል ሰባቱ በአገሪቷ አሉ በተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሩ ናቸው። ቶቶሪ ግን በደረጃቸው ከእነዚህ ከሚያንስ የሴቶች መካከለኛ ኮሌጅ ነው የተመረቁት።
አሁን አሁን መሻሻሎች ቢታዩም ሴቶች በከፍተኛ አመራርነት የሚሰሩባቸው አየር መንገዶች ቁጥር አነስተኛ ነው።
ቶቶሪ በዚህ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ከተሾሙ በኋላም አየር መንገዱ ከአንድ በመቶ በታች የሆኑትን በሴቶች የሚመሩ የጃፓን ትላልቅ ኩባንያዎችን ተቀላቅሏል።
“ራሴን እንደ የመጀመሪያዋ ሴት አለቃ አሊያም የመጀመሪያዋ የቀድሞ የበረራ አስተናጋጅ አላይም። እንደ አንድ ኃላፊነት እንዳለበት ግለሰብ ነው መሥራት የምፈልገው። እናም ብዙ ትኩረት አገኛለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር” የሚሉት ቶቶሪ፣ ነገር ግን ሕዝቡም ሆነ ሠራተኞቻቸው እንደዚያ እንደማያዩዋቸው መረዳታቸውን ይናገራሉ።
ቶቶሪ በዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የተመደቡት የጃፓን አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆች በማረፍ ላይ ከነበረው የባሕር ዳርቻ ጠባቂ አነስተኛ አውሮፕላን ጋር በተጋጨው አውሮፕላን ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች በሰላም እንዲወጡ በማስቻላቸው አድናቆት ከተቸራቸው ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር።
የበረራ ቁጥሩ 516 የሆነው የጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን በቶኪዮ ሃኔዳ አየር ማረፊያ በመንደርደሪያ ቦታ ከሌላ አውሮፕላን ጋር ከተጋጨ በኋላ በእሳት ተያይዞ ነበር።
በአደጋው በአንደኛው አውሮፕላን ውስጥ ከነበሩት ስድስት የበረራ ቡድን አባላት አምስቱ የሞቱ ሲሆን፣ አብራሪውም ጉዳት ደርሶበታል።
ሆኖም አውሮፕላኖቹ በተጋጩ በደቂቃዎች ውስጥ በኤርባስ ኤ350-900 አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው የነበሩት 379 መንገደኞች በሰላም መውጣት ችለዋል።
የአየር መንገዱ የበረራ አስተናጋጆችም ባከናወኑት ተግባር ልዩ ትኩረትን አግኝተው ነበር።
ቶቶሪም እንደ ቀድሞ የበረራ አስተናጋጅነታቸው የአቪየሽን ደኅንነት ምን ያህል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ በዚህ ክስተት በተግባር አይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቶቶሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ1985 የበረራ አስተናጋጅ ከሆኑ ከአራት ወራት በኋላም አደጋ አጋጥሞ ነበር።
አየር መንገዱ ያጋጠመው አደጋ በአቪየሽን ታሪክ ውስጥ በአንድ የአውሮፕላን አደጋ በርካታ ሰዎች የሞቱበት ነው።
በኦሱታካ ተራራ በደረሰው በዚህ አደጋ የ520 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
ቶቶሪ እንደሚሉት የአየር መንገዱ ሠራተኞች ወደ ተራራው በመውጣት አደጋውን ከሚያስታውሱ ሰዎች ጋር እንዲያወሩ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር።
“የአውሮፕላኑን ስብርባሪም የደኅንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ማዕከል አስቀምጠን፣ በመጽሐፍ እና በጽሑፍ ከምናነበው ባሻገር በዐይናችን በማየት እና በመዳሰስ ስለ አደጋው እንማር ነበር” ብለዋል።
አየር መንገዱ በ2010 በአገሪቷ ትላልቅ የንግድ ተቋማት ታሪክ ከፍተኛው ኪሳራ ካጋጠመው በኋላ በፍጥነት እየተለወጠ ነው።
በመንግሥት በሚደረግለት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በረራውን መቀጠል የቻለ ሲሆን፣ በቦርዱ እና በአስተዳደሩ ላይ ሰፊ ማሻሻያ ተካሂዷል።
አየር መንገዱ በኪሳራ ማጥ ውስጥ በገባበት ወቅት የታደጉት የ77 ዓመቱ ጡረተኛ እና የቡድሃ መነኩሴው ካዞ ኢናሞሪ ነበሩ።
እርሳቸው በአየር መንገዱ ላይ የአስተዳደር እና ሌሎች ማስተካከያዎችን ባያደርጉ ኖሮ እንደ ቶቶሪ ያሉ ግለሰቦች የአየር መንገዱ መሪዎች መሆናቸው የማይታሰብ ነበር።
ኢናሞሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ አየር መንገዱ ለደንበኞቹ ግድ የማይሰጠው ድርጅት ነው በማለት በድፍረት ተናግረው ነበር።
ድርጅቱ ለአብራሪዎች እና መሃንዲሶች እድገት የሰጠውም በእርሳቸው አስተዳደር ወቅት ነው።
“ድርጅቱ ራሱን እንደ የግል ድርጅት ስለማይቆጥር ተቸግሬ ነበር” ብለዋል ከሁለት ዓመታት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ ኢናሞሪ።
“በርካታ የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ወደ ድርጅቱ እጃቸውን ያስገቡ ነበር” ሲሉ የመንግሥት አካላት ጣልቃ ገብነት የተገደበ እንዳልነበር ተናግረዋል።
አየር መንገዱ ከእርሳቸው አስተዳደር ጊዜ ጀምሮ እንደገና ለማንሰራራት ብዙ ርቀት ተጉዟል።
የጃፓን መንግሥት በአገሪቷ የሴት አመራሮችን ቁጥር ለመጨመር ለአስር ዓመታት ሲጥር ቆይቷል።
በ2030 በዋና ዋና የንግድ ድርጅቶች ላይ ያለው የአመራርነት ቦታ ሲሶው ያህሉ በሴቶች እንዲያዝ ይፈልጋል። ይህን ዕቅድ ለማሳካት አልሞ የነበረው በ2020 የነበረ ቢሆንም እንዳሰበው ባለመሳካቱ ነው ለተጨማሪ አስር ዓመት ያራዘመው።
“ይህ በድርጅቶቹ አመራሮች የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ብቻ የሆነ አይደለም፤ ሴቶቹም የአመራርነት ቦታ ላይ ለመምጣት በራሳቸው መተማመናቸው ወሳኝ ነው” ይላሉ ቶቶሪ።
የእርሳቸው ሹመትም ሴቶች ደፍረው የማይሞክሩትን እንዲሞክሩ ያበረታታቸዋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።












