በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለመመለስ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚገባ ተገለጸ

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Ambassador Redwan Hussein Twitter

በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ለማስጀመር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ እንደሚገባ ተገለጸ።

እነዚህን መሠረተ ልማቶችን ለማስመለስ “አስቻይ የሆነ ሁኔታ በፍጥነት ለመፍጠር የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጉ አስፈላጊ” መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ያቋቋመው ተደራዳሪ ቡድን ገልጿል።

ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተቋቋመው የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻልም ዘንድ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ንግግሩን እንዲያስጀምር ጠይቋል።

የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ተወስኖ ንግግር እንዲጀመር ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም መገምገሙን ተገልጿል።

ከዚህም ንግግር በኋላ በሚደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ለማስጀመር አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረገም ነው ተብሏል።

“ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሲገባ በሚፈጠረው አስቻይ ሁኔታ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተቻለ ፍጥነት መልሶ ማቅረብ ይቻል ዘንድ፣ አስፈላጊ ቅደም ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን” ኮሚቴው ገልጿል። 

በትግራይ ሃይሎች ውስጥ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ የሰላም ኮሚቴውን መግለጫ “ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል የሚደረግ የማደናገሪያ ጨዋታ ነው” በማለት ውድቅ አድርገውታል።

አቶ ጌታቸው የፌዴራል መንግሥቱ “በተለያዩ ግንባሮች” ትንኮሳ አድርጓል ሲሉ ከሰዋል።

“ሁኔታውን የማዘግየት ስልቶችን ከመከተል በስተቀር ለሰላማዊ ድርድር ምንም ፍላጎት የላቸውም” በማለትም በዛሬው ዕለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ከትግራይ በተጨማሪ በአፋር እና በአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎች እየገጠማቸው ያለውን ችግር መቅረፍ እንደሚገባም በዚሁ መግለጫ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማድረስም ኮሚቴው አስቻይ የሆኑ ሁኔታ ለመፍጠር የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ ይገባል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊያደርስ የሚችል እንዲሁም ለቀጣይ የፖለቲካ ውይይቶችም የሰላም ምክረ ሃሳብ ላይ ውይይት በማድረግ የምክረ ሃሳብ ሰነድ በማዳበር ማጽደቁንም አስታውቋል።

ይህ ምክረ ሃሳብ ለአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ወኪል እንዲቀርብ መወሰኑም ተጠቅሷል።

ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደረገው ምንም አይነት ድርድር ሊመራ የሚችለው በአፍሪካ ኅብረት ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን በተደጋጋሚ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በኅብረቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ የገለጹት የትግራይ አመራሮች ድርድሩ በኅብረቱ ጥላ ስር ብቻ እንዲሆን እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

ማንኛውም ድርድር በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ሚና የተጫወቱትን የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ማካተት አለበት ብለዋል። 

ከዚህ ቀደምም የትግራይ አመራሮች የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ያላቸው ቅርበት እንዳሳሰባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

መንግሥት በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር የተዛመተውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጾ፣ ከእነዚህም ውስጥ የሰብዓዊነት ተኩስ አቁም ማወጅ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ እስረኞች መፍታትና የሰብዓዊ ድጋፍ በከፍተኛ ማሳለጥ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሰላም ውይይት ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመጀመር ዝግጁነት እንዳለው መግለጹንም ጠቁሟል።

ሆኖም ተቋርጠው የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን በተመለከተ የመንግሥታቸውን አቋም ያስታወቁት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ቀደም ሲል አገልግሎት ማስጀመር የሚቻልባቸው ሁኔታ መፍጠር እና የሰላም ንግግር መጀመር ቀዳሚ መሆን አለበት ብለው ነበር።

መሠረተ ልማቶች መመለስ እንደ ቅድመ ሁኔታ መወሰድ የለበትም ሲሉ የትግራይ አመራሮች በተደጋጋሚ ሲናገሩም ተሰምተዋል። በተጨማሪም በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ ሕይወትን የማዳን ጥያቄ ስለሆነ ክርክርም ሆነ ድርድር የሚደረግበት አይደለም ብለዋል።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ እና የአውሮፓ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች በአዲስ አበባ ካሉ ባለሥልጣናት እንዲሁም ከትግራይ አመራሮች ጋር መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚመለሱበትን ሁኔታ ተነጋግረዋል።

ልዑካኑ ትግራይ ደርሰው ከመጡ በኋላ በነዳጅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በማዳበሪያ ላይ ተጥሎ ያለው ክልከላ መነሳት አለበት ያሉ ሲሆን፤ በክልሉ ተቋርጠው የሚገኙ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሰው ለሚጠግኑ ባለሙያዎች ደኅንነት የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከትግራይ አመራር ለፌደራል መንግሥት ይዘው መመለሳቸውም ተመልክቷል።

ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ልዑካኑ ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ላይ አተኩረዋል ብሏል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ እና የተለያዩ አገራት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ባለፈው መጋቢት ወርም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቆ የህወሐት አመራሮችም ተቀብለውት ተቋርጦ የነበረው የረድኤት አቅርቦት ተጀምሯል ቢባልም በነዳጅ እጥረት ምክንያት መዳረስ እንዳልቻለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውንና ተደራዳሪ ወገኖችም መሰየማቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም።