እውቁ የሂፕ ሃፕ አቀንቃኝ ስኑፕ ዶግ ማጨስ ለማቆም ወስኛለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በከፍተኛ የማሪዋና ተጠቃሚነቱ የሚታወቀው እውቁ አሜሪካዊ አቀንቃኝ ስኑፕ ዶግ ዕጽ ማጨስ ለማቆም መወሰኑን አሳወቀ።
የሂፕ ሃፕ ሙዚቃ ኮከቡ ብዙዎችን ያስደነቀውን ውሳኔውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ይፋ አድርጓል።
“ብዙ ካሰብኩበት እና ከቤተሰብ ጋር ከተመካከርኩ በኋላ ማጨስ ለማቆም ወስኛለሁ” ብሏል።
ስኑፕ ዶግ ምን ከማጨስ እንደሚቆጠብ ያለው ነገር የለም። አንዳንዶችም አቀንቃኙ የሰጠው አስተያየት ፌዝ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
“ሊፍስ ባይ ስኑፕ” የተሰኘ የካናቢስ [ሃሺሽ] ምርቶች መሸጫ ኩባንያ ያለው አቀንቃኝ የሰጠውን አስተያየት መቀበል ያልቻለው አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ “ስኑፕ ያለ ጭስ ማለት ምድር ያለ ውሃ እንደማለት ነው” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
የእውቁ የሬጌ ሙዚቀኛ የቦብ ማርሊ ልጅ የሆነው ሮ ማርሊ ደግሞ “ከአሁን በኋላ በአጎቴ ቤት ሥጋ ጠብሰን ላንበላ ነው” ብሏል።
ሁሌም በጭስ ውስጥ ሆኖ የሚታየው ስኑፕ ከፍተኛው የካናቢስ አጠቃቀሙ በሙዚቃ ሥራዎቹ እና በሚሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ላይ ይታያል።
የ52 ዓመቱ ራፐር እአአ 1992 ላይ ያሳተመው የመጀመሪያው 'ዘ ክሮኒክ' የተሰኘው አልበሙ እንኳ መጠሪያው ከፍተኛ ጥራት ያለው ማሪዋና እንደማለት ነው።
ስኑፕ በበርካታ የሙዚቃ ሥራዎቹ ካናቢስ እንደሚያጨስ፤ ካናቢስ ማጨስ ጥሩ ስሜት ውስጥ እንደሚከት ብዙ ብሏል።
ስኑፕ ዶግ እአአ 2013 ላይ ከጂኪው መጽሔት ጋር በነበረው ቃለ መጠይቅ በቀን 80 የካናቢስ ጥቅሎችን እንደሚያጨስ ተናግሮ ነበር።
ማሪዋና በከፍተኛ መጠን መጠቀም ለጤና ችግር ሊያጋልጥ ይችላል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፀረ-አደንዛዥ ዕጽ አገልግሎት ከልክ በላይ ማሪዋና ማጨስ በሳምባ ካንሰር የመያዝ ዕድልን ከፍ ያደርጋል ይላል።
ከዚህ በተጨማሪ ማሪዋና ለረዥም ዓመታት የሚጠቀሙ ሰዎች ለጭንቀት፣ ምክንያታዊ ላልሆነ ከፍተኛ የፍርሃት ስሜት፣ እንቅልፍ ማጣት እና የምግብ ፍላጎት ማጣት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ቢቢሲ የስኑፕ ዶግ ተወካዮችን አግኝቶ ሙዚቀኛው ስለሰጠው አስተያየት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ሞክሮ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።












