በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ታጋቾች ወደ ጋዛ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ከስፍራው የተገኘ ቪዲዮ ማሳየቱን እስራኤል አስታወቀች

  2. በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ ደረሰ- የጋዛ ጤና ሚኒስቴር

    በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሰባተኛ ሳምንቱን በያዘው የጋዛው ጦርነት በእስራኤል የተቀናጁ ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 13 ሺህ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ ባደረሰው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 200 ታጋቾች ተወስደዋል።

    እስራኤል ምላሽ ነው ባለችው የማያባራ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን የጋዛ ሰርጥንም በሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብታታለች። መብራት፣ ውሃ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

  3. የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ታጋቾችን የማስለቀቅ ስምምነት ላይ 'መተማመን መጨመሩን' ተናገሩ

    ታጋቾች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር መስከረም መጨረሻ ላይ የተወሰዱ ታጋቾችን ለማስፈታት በሚደረገው ድርድር ላይ የሚቀሩ ችግሮች 'በጣም ጥቃቅን' እንደሆኑ ተናገሩ።

    መሃመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል 'እምነታቸው ከፍ ማለቱን' ነው ያስረዱት።

    በኳታር በሚደረገው ውይይት አሜሪካ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የስምምነት ውል እንዳቀረበች የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት ስምምነት ላይ እንደሚደረስም አስፍሯል።

    የዋይት ሐውስ የጸጥታው ምክር ቤት ቃለ አቀባይ አድሪያን ዋትሰን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እስካሁን ስምምነት ላይ እንዳልተደረሰ ጠቅሰው ነገር ግን "ስምምነት ላይ ለመድረስ ጠንክረን መስራታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ታጋቾች ከተለቀቁ ጦርነቱን በጊዜያዊነት ለማቆም እንደሚያስቡበት ቢናገሩም ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይደረስ አስታውቀዋል።

  4. ስድስት ሳምንታትን ያስቆጠረው የጋዛ ጦርነት የቅርብ ክስተቶች

    የጋዛ ጦርነት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ከአልሺፋ ሆስፒታል ውጡ ትዕዛዝ፦ የእስራኤል ጦር በተቆጣጠረው እና ከበባ ውስጥ ባስገባው የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል የአል ሺፋ ዳይሬክተር ጦሩ ህሙማኑን እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል። እስራኤል ይህንን ያስተባበለች ሲሆን ዳይሬክተሩ እንውጣ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ፈቃድ ሰጥቻለሁ ብላለች።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከአልሺፋ እየሸሹ ነው፦ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የእስራኤል ጦር ከተቆጣጠረው የጋዛ ሆስፒታል እየወጡ እና እየሸሹ ይገኛሉ። የእስራኤል መከላከያ ስራዊት በሆስፒታሉ እዝ ስር የሐማስ እዝ አለ በማለት ሆስፒታሉን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ፍተሻ እያደረገም ይገኛል። የሐማስ ዋሻ እና የጦር መሳሪያዎች ናቸው ያላቸውንም ምስሎች አሳይቷል።

    ተመድ ባቋቋመው የትምህርት ቤት መጠለያ የደረሰው ጥቃት፦እስራኤል ተመድ ባቋቋመው እና ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ በተቀየረ ትምህርት ቤት ባደረሰችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።እስራኤል ወደ መጠለያነት በተቀየረው ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ማድረሷን ባታረጋግጥም እየመረመርኩ ነው ብላለች።የሐማስ የጤና ባለስልጣናት በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች 80 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    የቆሰሉ ህጻናት ወደ አረብ ኤምሬትስ አቀኑ፦ 15 የሚደርሱ የተጎዱ ፍልስጤማውያን ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸውን ያሳፈረው የመጀመሪያው አውሮፕላን አቡዳቢ ደርሷል። የተበባሩት አረብ ኤምሬቶች ባለስልጣናት በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ 1 ሺህ ፍልስጤማውያን ህጻናት እና ሴቶችን ከጋዛ አስወጥቶ በአገሩ ወደሚገኙ የጤና ማዕከላት ለማምጣት ማቀዱን አስታውቋል።

    ወደ እየሩሳሌም የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ፦ በሐማስ የተወሰዱ ከ200 በላይ ታጋቾች ቤተሰቦች እና ደጋፊዎቸቻቸው ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም በመሄድ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በርካቶች መፈክሮችን እና ሰንደቅ አላማም ይዘው ነበር። አንዳንዶችም የታገቱትን ሰዎች ምስል ይዘው የነበረ ሲሆን ታጋቾችን ለማስለቀቅ የእስራኤል መንግሥት የተቻለውን እያደረገ አይደለም ሲሉም ተሰምተዋል።

  5. እስራኤል ተመድ ባቋቋመው የትምህርት ቤት መጠለያ ባደረሰችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸው ተነገረ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል ተመድ ባቋቋመው እና ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ በተቀየረ ትምህርት ቤት ባደረሰችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    እስራኤል ወደ መጠለያነት በተቀየረው ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ማድረሷን ባታረጋግጥም እየመረመርኩ ነው ብላለች።

    የሐማስ የጤና ባለስልጣናት በሰሜን ጋዛ ጃባሊያ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች 80 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።

    ቢቢሲ በጃባሊያ አል ፋክሁራ ትምህርት ቤት የተቀረጸ ቪዲዮን ያገኘ ሲሆን በከፋ የተጎዱ እና እንቅስቃሴ አልባ ሰዎችንም በወለሎች ላይ ተኝተው ያሳያል።

    በቪዲዮው ላይ ከ20 የሚበልጡ ተጎጂዎች የሚታዩ ሲሆን ያሉበትም ክፍል ህንጻ በከባዱ እንደተጎዳ ያሳያል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ ወደ መጠለያነት በተቀየረው ትምህርት ቤታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ጠቅሰው "በርካታ የተገደሉ እና የተጎዱ ሰዎችን የሚያሳዩ ዘግናኝ ቪዲዮዎችን እና ምስሎችን ማየታቸውን" ተናግረዋል።

    በጃባሊያ ሌላ ስፍራ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ ከ30 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

  6. በመቶዎች የሚቆጠሩ ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ሲሸሹ፤ በርካቶች በመጠለያ ጣብያ ውስጥ ተገደሉ

  7. የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ 'የሞት ቀጠና' ሆኗል- የዓለም ጤና ድርጅት

    የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የእስራኤል ጦር የተቆጣጠረው የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አል ሺፋ 'የሞት ቀጠና' ሆኗል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

    የቦምብ ድብደባዎችን ባስተናገደው ሆስፒታሉ መግቢያ ላይ " የጅምላ መቃብር" ማየቱን እና በስፍራው ከ80 በላይ ሰዎችም ተቀብረዋል መባሉንም ተቋሙ አስታውቋል።

    የጤና ተቋሙን ሁኔታ የገመገመው የዓለም ጤና ድርጅት ሁኔታውን 'ተስፋ አስቆራጭ' ሲል ጠርቶታል።የእስራኤል ጦር በሆስፒታሉ ስር የሐማስ የእዝ ማዕከል አለ በሚልም ወረራ የፈጸመ ሲሆን ለቀናትም ያህል ፍተሻ እያደረገ ይገኛል።

    ሆስፒታሉ የቦምብ ድብደባ እና የተኩስ ልውውጦችንም ማስተናገዱን መረጃዎች አግኝቻለሁ ብሏል። ሆስፒታሉ መብራት፣ ውሃ እና ነዳጅ የተቋረጠበት ሲሆን በዚህም በርካቶች መሞታቸው ተገልጿል።

    በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንም ከአልሺፋ ሆስፒታል ወጥተው በእግራቸው እየሸሹ ይገኛሉ።

    አንዳንዶችም በመንገዳቸው ላይ ነጭ ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡም የሚያሳዩ ፎቶዎች ታይተዋል። ከሆስፒታሉ ከወጡት መካከል የሆነው አንድ ጋዜጠኛ እንደተናገረው ሌሊት ላይ የተኩስ ድምጽ እና ፍንዳታዎች ነበሩ ብሏል።

    በተጨማሪም የእስራኤል ቡልዶዘሮች በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ትላልቅ ጉድጓዶች መቆፈራቸውንም ተናግሯል።

  8. እስራኤል በሐማስ የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን ለማግኘት ንስርን እንዴት ተጠቀመች?

  9. በርካቶች ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ለቀው ሲወጡ የተወሰኑት እዚያው ቀርተዋል

    አል-ሺፋ ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, AHMED EL MOKHALLALATI

    በእስራኤል ወታደሮች ከቀናት በፊት ከተወረረው የጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አል-ሺፋ በርካታ ሰዎች ነጭ ጨርቅ እያሳዩ ጊቢውን ለቀው መውጣታቸውን በሆስፒታሉ ውስጥ ያለ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናገረ።

    ጋዜጠኛ ኻዴር አል ዛኑን እንዳለው ከቀናት በፊት የእስራኤል ወታደሮች በሆስፒታሉ ውስጥ አሰሳ ሲያካሂዱ ከባድ ተኩስ እና ምርመራ መካሄዱን ገልጿል።

    “ሆስፒታሉ መንቀሳቀስ ከማይችሉት ሕሙማን እና ከጥቂት ዶክተሮች በስተቀር ሁሉም ሰው ቀደም ብሎ ለቆ ወጥቷል” ብሏል።

    በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአል-ሺፋ ሆስፒታል ዛሬ ጠዋት በእግራቸው ለቀው ወጥተዋል ስለማለቱ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    ጨምሮም በአሁኑ ወቅትም 120 ቁስለኛ ህሙማን ቁጥራቸው ካልተገለጸ ከጊዜያቸው ቀድመው ከተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት ጋር በሆስፒታሉ ውስጥ ይገኛሉ።

    ቀደም ሲል የጤና ባለሥልጣናት ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “450 የቆሰሉ እና በጽኑ የታመሙ” መንቀሳቀስ የማይችሉ ህሙማን እነሱን ከሚመከታተሉ የተወሰኑ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በሆስፒታሉ ይቆያሉ ብለው ነበር።

    የተጠቀሱትን አሃዞች ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልቻለም።

  10. ፍልስጤማውያን ከደቡባዊ የጋዛ ክፍሎች ለቀው እንዲወጡ እስራኤል አዘዘች

    በእስራኤል የአየር ጥቃት የወደመ ሕንጻ ኻን ዩኒስ ውስጥ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል የአየር ጥቃት የወደመ ሕንጻ ኻን ዩኒስ ውስጥ

    ፍልስጤማውያን በደቡባዊ ጋዛ ከሚገኘው የኻን ዩኒስ አካባቢ ለቀው እንዲወጡ እስራኤል አዲስ ባወጣችው ትዕዛዝ አስጠነቀቀች።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ አማካሪ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ ኤምኤስኤንቢሲ ለተባለ የአሜሪካ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

    “ለሰዎቹ ቀላል እንደማይሆን አውቃለሁ፣ ነገር ግን ሲቪሎች በተባራሪ ጥይት መካከል ጉዳት እንዲደርስባቸው አንፈልግም” ብለዋል አማካሪው።

    ጦርነቱ እንደጀመረ ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ ነዋሪዎች ከሰሜናዊ ጋዛ ለቀው እንዲወጡ በእስራኤል መታዘዙን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ደቡብ መውጣታቸው ይታወቃል። ነገር ግን ደቡባዊው የጋዛ ክፍልም በእስራኤል ከባድ ጥቃት ውስጥ ነው የቆየው።

    አስራኤል ከሦስት ቀናት በፊት የኻን ዩኒስ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ የሚያስጠነቅቁ መልዕክቶችን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን የበተነች ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ሌላ ማስጠንቀቂያ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተላልፏል።

    ኻን ዩኒስ በደቡባዊ ጋዛ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ትልቁ ሲሆን፣ የእስራኤልን ጥቃት በመሸሽ ከሰሜናዊ ጋዛ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙበታል።

    በከተማዋ ሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ ሲሆን፣ የእስራኤልን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ወታደራዊ ዘመቻ በኻን ዩኒስ ላይ መካሄዱ አይቀሬ ነው ተብሏል።

  11. በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሕጻናትን ጨምሮ የ40 ሰዎች ሕይወት አለፈ

    በአል-ሺፋ ያሉ ታካሚዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በአል-ሺፋ ያሉ ታካሚዎች

    የተባበሩት መንግሥታት አል-ሺፋ ሆስፒታል በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያት 4 ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ የ40 ታማሚዎች ሕይወታቸው ማለፉን አስታወቀ።

    የሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች በእስራኤል ጦር ተደጋጋሚ ድብደባ ሲደርስበት የነበረው እና በጦሩ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ሆስፒታል ባለፉት 7 ቀናት የሟች ታማሚዎች ቁጥር 44 መሆኑን ተናግረዋል።

    የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋዛን በተመለከተ ባወጣው ዕለታዊ ሪፖርት መሠረታዊ አቅርቦቶች በቀሟጠጡባት ጋዛ በውሃ ጥም እና በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች ስለመኖራቸው ሪፖርት እየደረሰኝ ነው ብሏል።

  12. እስራኤል በቀን ሁለት ቦቴ ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዲገባ እፈቅዳለሁ አለች

    ነዳጅ

    እስራኤል በአሜሪካ የደረሰባትን ጫና ተከትሎ በየቀኑ ሁለት ቦቴ ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ አስታወቀች።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ በየሁለት ቀኑ 140ሺህ ሊትር ነዳጅ ጋዛ እንዲገባ ይፈቃል ብለዋል።

    አብዛኛው ነዳጅ ጥቅም ላይ የሚውለው እርዳታ ለሚያጓጉዙ ደረቅ ተሸከርካሪዎች እና የተባበሩት መንግሥታት የንጹህ ውሃ አቅርቦት እና ንጽህና ሥራን ለማስኬድ ነው።

    የተቀረው ደግሞ በነዳጅ እጥረት የተቋረጠውን የሞባይል እና ኢንተርኔት አገልግሎትን ለማስቀጠል ጥቅም ላይ ይውላል።

    ተመድ በነዳጅ እጥረት እና የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት አማራጮች አለመኖር አግልግሎቴን ለማቆም ተገድጃለሁ ብሎ ነበር።

    እስራኤል በጋዛ የተደበቀ የተከማቸ ነዳጅ አለ ብላ የምትከራከር ሲሆን ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዲገባ የምፈቅደው ታጋቾች ነጻ ሲወጡ መሆን አለባት ስትልም ቆይታለች።

  13. በሐማስ ታግቶ የነበረው ታንዛኒያዊ መገደሉ ተረጋገጠ

    የታንዛኒያ ዜጋ

    የፎቶው ባለመብት, MASHAV ISRAEL

    የታንዛኒያ መንግሥት በሐማስ ታግቶ የነበረው ዜጋው መገደሉን ይፋ አደረገ።

    ክሌመንስ ፌሊክ ምቴንጋ የተባለው የ22 ዓመት ወጣት ታንዛኒያዊ ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ነበር ከሌላ የአገሩ ዜጋ ጋር ታግቶ የነበረው።

    በእስራኤል የግብርና ትምህርት ሲከታተል የነበረው ምቴንጋ እንዴት ሕይወቱ ሊያልፍ እንደቻለ የተባለ ነገር የለም።

    የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የቀሪውን ታጋች ታንዛኒያዊ ዕጣ ፈንታ በተመለከተ እና የሟቹን አስክሬን ወደ አገር ለማምጣት ከእስራኤል መንግሥት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል።

    በእስራኤል ወደ 260 የሚጠጉ የግብርና ትምህርት የሚከታተሉ ታንዛኒያውያን ተማሪዎች ይገኛሉ።

    ሐማስ መስከረም 26 ላይ ከ230 ያላሱ ሰዎችን ከእስራኤል አግቶ ወደ ጋዛ መውሰዱ ይታወሳል።

  14. ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ከጋዛ የወጡ ምስሎች

    ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ጋዛ ያለችበትን ሁኔታ የሚያሳዩ ምስሎች በዜና ወኪሎች ተልከዋል።

    ምስሎቹ የእስራኤል ጦር በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻውን ስለማስቀጠሉ ያሳያሉ።

    በደቡባዊ ጋዛ ካን ዩኒስ በጥቃት ከወደመ ተሸከርካሪ ጎን የሚራመድ ፍልስጤማዊ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በደቡባዊ ጋዛ ካን ዩኒስ በጥቃት ከወደመ ተሸከርካሪ ጎን የሚራመድ ፍልስጤማዊ
    በደቡብ ጋዛ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በደቡብ ጋዛ የወደመ ሕንጻ
    ሰሜናዊ ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ሰሜናዊ ጋዛ
    በኢንዶኔዢያው ሆስፒታል ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጣቸው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በኢንዶኔዢያው ሆስፒታል ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጣቸው
  15. በምስል፡ የእስራኤል ጦር በጋዛ

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰሜናዊ ጋዛ የሚያደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክሮ ቀጥሏለ።

    ጦሩ የሠራዊቱ አባላት በጋዛ ሆነው ዘመቻ ሲያካሂዱ የሚያሳዩ ምስሎችን ለመገናኛ ብዙሃን አጋርቷል።

    በአሁኑ ወቅት በተለይ በሰሜናዊ ጋዛ የግንኙነት መስመሮች ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው ከስፍራው መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

    የእስራኤል ሠራዊት አባላት በሰሜናዊ ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Israeli Defense Forces

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ሠራዊት አባላት በሰሜናዊ ጋዛ
    የእስራኤል ሠራዊት አባል በሰሜናዊ ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Israeli Defense Forces

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ሠራዊት አባል በሰሜናዊ ጋዛ
    የእስራኤል ሠራዊት አባላት በሰሜናዊ ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Israeli Defense Forces

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ሠራዊት አባላት በሰሜናዊ ጋዛ
  16. ተመድ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ማድረስ አልቻልኩም አለ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ዓርብ ለማድረስ የታቀውን የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ አልቻልኩም አለ።

    በጋዛ ለሁለተኛ ቀን የሞባይል ስልክ፣ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት፣ ዋይፋይ እንዲሁም መደበኛ የስልክ መስመሮች ተቋርጠው ይገኛሉ።

    በጋዛ የተመድ ተወካይ ጁሊዬት ቱማ በጋዛ ካሉ ሠራተኞቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን ገልጸው፤ የግንኙነት አማራጮች እና የነዳጅ አቅርቦት ቢኖር እርዳታ ማድረስ ይቻላናል ብለዋል።

    የእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ከተጀመረ በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነዳጅ ወደ ጋዛ እንዲገባ እስራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ መፍቀዷ ይታወሳል።

    ይህ ነዳጅ ግን በፍጥተን እለቋል።

    የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በጋዛ የምግብ አቅርቦት የለም የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጸ ሲሆን የጋዛ ነዋሪዎች የመራብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል።

  17. የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ በሽታ በፍጥነት እየተሰራጨ ነው አለ

    ጋዛ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ሰዎች በመጠላያ ጣቢያዎች ተጨናንቀው መኖራቸው በሽታ ከተገመተው ፍጥነት በላይ እየተሰራጨ ነው አለ።

    ድርጅቱ ከ70ሺህ በላይ የመተፈንሻ ስርዓት ሕመም እና ከ44ሺህ በላይ የተቅማጥ በሽት ኬዞችን መመዝገቡን ገልጾ የቀዝቃዛማ ወራት መግቢያ መቃረቡ ደግሞ ሁኔታውን የበለጠ አሳሰቢ ያደርገዋል ብሏል።

    “የቀዝቃዛ ወራት እየቀረቡ ባለበት ወቅት የበሽታ ስርጭቱ እጅጉን አሳስቦናል” ብለዋል በጋዛ እና ዌስት ባንክ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ሪቻርድ ፒፕርኮርን።

    በጋዛ የነዳጅ እጥረት የውሃ ማጣሪያ ማሽኖች ስራ እንዲያቆሙ በማድረጉ ሰዎች የተበከለ ውሃ ለመጠጣት በመገደዳቸው ለተቅማት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸውን ከፍ አድርጎታል ተብሏል።

    በጋዛ ቆሻሻ የመሰብሰብ ስራም በመቆሙ በሽታ ተሸካሚ የሆኑ ተባዮች እና አይጦች እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

  18. ኔታኒያሁ ለሰላማዊ ሰዎች ሞት ምክንያት ሐማስ ነው አሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እስራኤል በጦርነቱ የሰላማዊ ሰዎች ጉዳትን ለመቀነስ ብትጥርም ስኬታማ አልሆነችም አሉ።

    ጠቅላይ ሚንስትሩ አገራቸው ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ብታደርግም “ሐማስ ግን የተቻለውን በማድረግ ለጉዳት እየዳረጋቸው ነው” ሲሉ ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

    ኔታኒያኑ እንደሚሉት እስራኤል በራሪ ወረቀቶችን በመበተን እና የስልክ ጥሪ በማድረግ ሰላማዊ ሰዎች ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ እንዲያመሩ የምትገልጽ ቢሆንም ሐማስ ግን ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው ከሚባለው ቦታ ላይ ሆኖ ይተኩሳል ብለዋል።

    በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚንስቴር መስከረም 26 በጀመረው ጦርነት እስካሁን በእስራኤል ጥቃት ከ11ሺህ 500 በላይ ሰዎች በጋዛ መገደላቸውን አስታውቋል።

  19. ሕይወት በጋዛ፡ "ጦርነቱ መቶ ዓመታትን ወደኋላ መልሶናል"

  20. እስራኤል የሁለተኛዋን ታጋች አስክሬን በጋዛ ማግኘቷን አስታወቀች

    ኖራ ማርሲያኖ

    የፎቶው ባለመብት, IDF

    የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የ19 አመቷን ታጋች ወታደር አስከሬን በጋዛ ማግኘቱን ገልጿል።

    የእስራኤላዊቷ ኖራ ማርሲያኖ አስከሬንም የተገኘው በጋዛ ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ አጠገብ በሚገኝ ስፍራ እንደሆነም ጦሩ አስታውቋል።

    ወታደሯ መሞቷ ከተገለጸ ከቀናትም በኋላ ነው አስከሬኗ የተኘው።

    ወታደሯ ሐማስመስከረም 26 በእስራኤልላይጥቃትበፈጸመበትወቅትከተወሰዱ 200 ታጋቾችመካከልአንዷነበረች።

    አስከሬኗ ወደ እስራኤል ከተወሰደ በኋላም ማንነቷን የሚያረጋግጡ ምርመራዎች መካሄዳቸው ተገልጿል።

    እስራኤል በትናንትናው ዕለት በአልሺፋ አጠገብ በሚገኝ ስፍራ ይሁዲት ዌይስ የተባለችው ታጋች አስከሬን ተገኝቷል ብላለች።