በሙስናና በሕግ ጥሰት የሚወነጀሉት የኬንያ ፖሊሶች ደሞዝ ሊጨመርላቸው ነው

የኬንያ ፖሊስ አባል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የኬንያ መንግሥት በጭካኔው እና በሙስና ለሚታወቀው የፖሊስ ኃይሉ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ሊያደርግ ነው።

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለፖሊስ እና ለማረሚያ ቤት ጠባቂዎች በቀጣይ ሦስት ዓመታት የ40 በመቶ የደሞዝ ጨማሪ እንደሚደረግ ይፋ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህ የደሞዝ ጭማሪ የሚደረገው የጸጥታ አስከባሪዎቹን ተነሳሽነት ለመጨመር እና ደኅንነት ለማጠናከር ነው ብለዋል።

የኬንያ ፖሊስ አባላት በአገሪቱ ጥሩ ስም ባይኖራቸውም የዝቅተኛ ሕይወት ኑሯቸው ግን መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም።

የፖሊስ አባላት ክፍያ ያነሰ ከመሆኑ የተነሳ የፖሊስ አባላቱ በወንጀል ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙበት አጋጣሚ በርካታ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት እራሳቸውን የሚያጠፉ የፖሊስ ኃይል አባላት ቁጥር ከፍ ማለት ከአእምሮ ጤና ከኑሮ ደረጃ ማነስ ጋር ሲያያዝ ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ የደሞዝ ጭማሪውን ይፋ ሲያደርጉ ለጸጥታ ኃይል አባላቱ የደሞዝ ጭማሪ መደረጉ “ሞራላቸውን ከፋ ከማድረጉም በላይ የኬንያውያንን ደኅንነት የበለጠ መጠበቅ ያስችላል” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በፖሊስ አገልግሎት ውስጥ የሚስተዋለው ሙስናንን ከመሠረቱ ለመቅረፍ ትኩረት እንደሚሰጡ ጨምረው ተናግረዋል።

የደሞዝ ጭማሪው እና ሌሎች በሂደት ላይ ያሉ የአሰራር ለውጦች በፖሊስ ኃይል ውስጥ ያለው የአመራር ድክመት፣ ሙስና እና ተቋማዊ ድክመትን ለይቶ ያወጣል ብለዋል ፕሬዝዳንት ሩቶ።

በአሁኑ ወቅት በኮንስታብል ደረጃ ኃይሉን የሚቀላቀል አዲስ ቅጥረኛ መነሻ ደሞዙ 17ሺህ የኬንያ ሽልንግ (110 የአሜሪካ ዶላር) ገደማ ነው።

በአዲስ መልክ ይተገበራል በተባለ አሰራር የፖሊስ ኃይልን የሚቀላቀሉ ኬንያውያን የዕድሜ ጣራ ከ18 ወደ 21 ከፍ እንዲል ይደረጋል ተብሏል።