የዩክሬን ጦር በደቡብ በኩል የሩሲያ ኃይል ላይ ጥቃት ከፈተ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን ጦር በደቡባዊ ዛፖራዝሂያ ግዛት ላይ ባለው የሩስያ ኃይል ላይ ጥቃት መክፈቱን የሩስያ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ዛፖሪዝሂያ በደቡብ በኩል ቁልፍ የምትባል ግዛት መሆኗም ተነግሯል።
የዩክሬን ወታደሮች በታንክ፣ በመድፍ እና በሰው አልባ አውሮፕላኖች ተደግፈው በደቡባዊቷ ኦሪኪቭ ከተማ እየገሰገሱ ሲሆን ይህም ለሁለተኛ ምሽት መቀጠሉም ተነግሯል።
የዩክሬን መከላከያ ከፍተኛ ባለስልጣን “ጠላት” ብለው የጠሩት የሩሲያ ኃይል “በንቃት እየተከላከለ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የዩክሬን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የመልሶ ማጥቃት ትኩረት የዛፖሪዝሂያ ግዛት እንደምትሆን በርካታ ወታደራዊ ባለሙያዎች ሲናገሩም ነበር።
በባለሙያዎቹ ትንተና መሰረት ዩክሬን የአዞቭ ባህር ላይ በመድረስ በግዛቲቷ ውስጥ የሚገኙትን የሩሲያ ኃይሎች ለሁለት በመክፈል መነጣጠልም አቅዳለች ብለዋል።
ይህም ከተሳካ የሩስያን የውጊያ አቅም ከማዳከም ባለፈ ሩሲያ በህገወጥ መንገድ ጠቅልላታለች የምትባለውን ክሪሚያ ግዛትም የሚወስደውን የመሬት ድልድይ መዳረሻ ያሳጣታል።
ዩክሬን መልሶ ማጥቃት ለወራት ስታዘጋጅ የቆየች ሲሆን ወታደሮቿን ለማሰልጠን እንዲሁም የላቁና የተራቀቁ ወታደራዊ መሳሪያዎችን ከምዕራባውያን አጋሮችም ለመቀበል ጊዜዋን ፈጅታለች።
የዩክሬን መንግሥት ስለ ወታደራዊው እቅድም ዝምታን የመረጠ ቢሆንም ጦሩ በበርካታ ግንባሮች ውጊያን በመክፈት የሩሲያን ኃይል ድክመት እየፈተሸ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ቀጥሏል።
በዋና ከተማዋ ኪዬቭ በስተምዕራብ በምትገኘው ዛይቶሚር ወስጥ የሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ጥቃቶች በምሽት መፈጸማቸው ተገልጿል። በነዚህ በተፈጸሙ ጥቃቶችም የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ተብሏል።
ከሰሞኑም የዩክሬን መከላከያ፣ ሩሲያ በአገሪቱ የሚገኝ ትልቅ ግድብን ደብድባ ጉዳት እንዳደረሰች ገልጿል።
በሞስኮ ቁጥጥር ሥር በወደቀው የዩክሬን ደቡባዊ ግዛት የሚገኘው ይህ ግድብ በሩሲያ ጥቃት ደርሶበታል ተብሏል።












