የኢትዮጵያን የሰላም ስምምነት የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን ቆይታ ተራዘመ

የአፍሪካ ህብረት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድን ከ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክ ሃመር ጋር

የፎቶው ባለመብት, @USEmbassy Addis

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነትን የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ የባለሙያዎች ቡድን የቆይታ ጊዜ መራዘሙ ተገለጸ።

የአፍሪካ ኅብረት የስምምነቱን ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴም የቆይታ ጊዜ እስከ መጪው ዓመት ታኅሣሥ ወር ድረስ ማራዘሙን በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ረቡዕ ግንቦት 30/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተደረሰው ስምምነት የአፍሪካ ኅብረት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ የባለሙያዎች ቡድን ዋነኛ አካል ነው።

ከህወሓት እና ከፌደራል መንግሥት የተውጣጡ፣ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ኅብረት በከፍተኛ ደረጃ ፓነል የሚመራ የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

የዚህን ኮሚቴ የሥልጣን ጊዜንም አስመልክቶ የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 11 ከተሰማሩበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት እንደሚቆይ ተጠቅሷል።

ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች ከተስማሙ የቆይታ ጊዜው ሊራዘም እንደሚችልም ሰፍሯል።

የኅብረቱ የተቆጣጣሪ እና አረጋጋጭ ቡድን የሚመራው በኬንያው ጄኔራል ስቴፈን ራዲና ሲሆን ናይጄሪያዊው ኮሎኔል ሩፋይ ኡመር ማይሪጋ እና ደቡብ አፍሪካዊው ኮሎኔል ቴፎ ሴኮሌንም በአባልነት ይዟል።

ኮሚቴው ህወሓት እና መንግሥትን ባሸማገሉት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ታኅሣሥ 20/2015 ዓ.ም. በመቀለ ይፋ ሥራ መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።

በወቅቱ የኅብረቱ ተልዕኮ ቡድን ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ለሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መሠረታዊ እርምጃ መሆኑን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቆ ነበር።

በቅርቡም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክ ሐመር ከኮሚቴው አባላት ጋር በመቀለ መገናኘታቸው፣ እንዲሁም ከመሪው ጄኔራል ራዲና ጋር በአዲስ አበባ መገናኘታቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

የኮሚቴው የጊዜ ቆይታ መራዘሙም ለዘላቂ ሰላም ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጥቀስ አሜሪካ በበጎ እንደምትቀበለውም መጠቀሱ ተገልጿል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር በመቀለ ቆይታቸው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ላይ የተደረሰውን ሂደት እና ያጋጠመው ተግዳሮቶች ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።

በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ምዕራብ ትግራይ የመመለስን ሂደትን በተመለከተ ሁለቱም አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን የክልሉ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

በተጨማሪም የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግበራዊ እንዳይሆን የኤርትራ መንግሥት ስለደቀነው ችግርም መወያየታቸውም ተገልጿል።

በዚሁም ውይይት ላይ ለትግራይ የሚላከው እርዳታ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ውሏል መባሉን አስመልክቶ በተደረገው ምርመራ ላይ ለልዑካኑ ገለጻ የተደረገ ሲሆን የግኝቶቹን ዋና ዋና ነጥቦችም ማጋራታቸውም ተገልጿል።

የምርመራው ግኝቶቹ በቅርቡ ይፋ ተደርጎ ተጠያቂነት እንደሚረጋገጥ እና የተቋረጠው እርዳታንም አሜሪካ እንድታስቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከግንቦት 23 እስከ 29/2015 ዓ.ም. ለሰባት ቀናት በኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ቆይታ አድርገዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሽግግር ፍትሕ እና የተጠያቂነት ጉዳይን እንዲሁም ትጥቅ ማስፈታትን፣ ተዋጊዎችን መበተን እና መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ የስምምነቱ አተገባበር ሂደትን እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች እንደሚያነሱ ተጠቅሶ ነበር።

ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ጋር ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመርን ጨምሮ ከአሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ጋር የነበረው ውይይት ያተኮረው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ላይ መሆኑም ተገልጿል።

በቀጣይም በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመስራት ተስማምተዋል ቢልም የሰላም ስምምነቱ ስለደረሰበት ደረጃ መወያየታቸው አልተገለጸም።

ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን የቀጠፈውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ከሰባት ወራት በፊት መደረሱ ይታወቃል።

የሰላም ስምምነት መሠረት ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መጀረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ሆኖም በክልሉ ያሉት የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል አለመውጣታቸው እና በክልሉ በሚፈጸሙ ጥሰቶችም ስማቸው ሲጠቀስ ይሰማል።