ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ኃይሎች በመቀለ የድሮን ጥቃት ተፈጸመ ሲሉ ከሰሱ
የትግራይ ኃይሎች በመቀለ ከተማ ዛሬ መስከረም 03/2015 ዓ.ም. ጠዋት መንግሥት አዲስ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ ከሰሱ።
የትግራይ አመራሮች አስቸኳይና በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ግጭት ለማቆም ዝግጁ መሆናቸውን ካስታወቁ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት መድረሱ የተገለጸው።
መንግሥት ለቀረበበት የድሮን ጥቃት ክስ አስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ከአምስት ወራት የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ አገርሽቶ ሦስት ሳምንታትን አስቆጥሯል።
የትግራይ ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ የድሮን ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የመቀለ ዩኒቨርስቲን አዲ ሃቂ ካምፓስ መሆኑን ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
በትግራይ ክልል ባለው ስልክን ጨምሮ የትኞቹም የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም።
አቶ ጌታቸው “በፌደራል መንግሥቱና በኤርትራ መንግሥት በብዙ ግንባሮች የተከፈተው ከፍተኛ የማጥቃት ዘመቻ በመክሸፉ በሰላማዊ ዜጎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ የበቀል እርምጃ ነው” ብለውታል ተፈጸመ ያሉትን የአየር ጥቃት።
ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ ጉዳት የደረሰበት ነው የተባለ ግለሰብ እዚያው መቀለ ወደ ሚገኘው አይደር ሆስፒታል እንደገባ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረ ሥላሴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ድርድር ትግራይን ወክለው እንዲደራደሩ ከተሰየሙት አንዱ ናቸው።
ከአቶ ጌታቸው በተጨማሪ የቀድሞ ኢትዮጵያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳይ ለመደራደር ተሹመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ማስታወቁ ይታወሳል።
የትግራይ አመራሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚደረገው የሰላም ሂደት ላይ ለመሳተፍና ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ አልሰጠም።
ለድርድር ሂደቱ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር አስቸኳይና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆምም እንደሚስማሙ ገልጸዋል።
የትግራይ አመራሮች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ባመለከቱበት መግለጫ ላይ በኅብረቱ በሚመራው ድርድር ላይ ተአማኒነት ያለው የሰላም ሂደት እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ ጨምረውም በሂደቱ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያላቸው አሸማጋዮች፣ መተማመንን የሚፈጥሩ ታዛቢዎች እና ምክር እና ድጋፍ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲካተቱ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ የትግራይ አመራሮች የሰጡትን መግለጫ በደስታ ተቀብለዋል።በመጪው ጥቅምት ወር ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ የሚታወስ ነው።
በጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ የሚገመት ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ለተረጂነት መዳረጋቸውን የመንግሥታቱ ድርጀት መረጃ ያመለክታል ።
ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ሁለቱም ወገኖች ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ጦርነቱም በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን የሚከስ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።