የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ እና አውሮፓ የተኩስ አቁም ጥሪውን ደገፉ

የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ቆሞ ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥት፣ የአውሮፓ እና የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔውን በበጎ እንቀበለዋለን አሉ።

የትግራይ ኃይሎች እሁድ መስከረም 01/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ አስቸኳይ እና በጋራ ስምምነት ተኩስ ለማቆም እንደሚስማሙ እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሰላም ድርድር ሂደት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የትግራይ ክልል መንግሥት በአስቸኳይ ግጭት ለማቆም እና የሰሜን ኢትዮጵያውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ዝግጁ ነን ማለታቸውን በአውንታዊነት ተመልክተውታል ሲሉ ቃል አቀባያቸው ገልጸዋል።

ዋና ፀሐፊው የጦርነቱ ተሳታፊዎች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ሳይዘገዩ በቅን ልቦና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ንግግር እንዲጀምሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ቃል አቀባያቸው አመልክተዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰላም ድርድር ድጋፉን እንደሚሰጥ አረጋግጠው ለመላው ኢትዮጵያውን መልካም አዲስ ዓመት ተመኝተዋል።

የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ለሚደረግ የሰላም ንግግር ቁርጠኛ መሆናቸው በበጎ ጎኑ እቀበለዋለሁ ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ናቸው።

ሊቀ መንበሩ ይህ መልካም አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ልዩ ዕድል ነው ያሉ ሲሆን፤ ሁለቱም ተዋጊ ወገኖች በአስቸኳይ ተኩስ ለማቆም እና በቀጥታ ንግግር ለማድረግ እንዲጀምሩ ጨምረው አሳስበዋል።

አሜሪካ በበኩሏ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንደምትቆም እና የሕዝቡን ሰላም እና የምጣሄ ሃብት እድገት የሚያረጋግጥ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንደምትደግፍ ገልጻለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት፤ “በየትኛውም ስፍራ፣ በየትኛውን ጊዜ” ለሰላም ዝግጁ ነኝ ማለቱን አስታውሶ፤ የትግራይ ኃይሎችም ግጭት አቁመን ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ ነን ማለታቸው የሚበረታታ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው፣ የትግራይ ክልል መንግሥት ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ለንግግር ዝግጁ መሆኑን የገለጸበትን መልካም አጋጣሚ ሁሉም ወገኖች እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።

የተኩስ ድምጽ የማይሰማበት ዓመት

የትግራይ ኃይሎች በኢትዮጰያውያን የዘመን መለወጫ በዓል ዕለት ባወጡት መግለጫ ተኩስ ለማቆም ዝግጁ ከመሆናቸው በተጨማሪ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ተኩስ የማይሰማበት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችና የሰብዓዊ እርዳታ ያለ ገደብ የሚደርሱበት እንዲሆን ፍላጎታቸውን መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሓት መግለጫን ተከትሎ ከፌደራሉ መንግሥት እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ግጭቱን ያለምንም ቅድመ ሆኔታ በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲግልጽ ነበር።

ለዚህም ከጥቂት ወራት በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣንት የተካተቱበት ተደራዳሪ ኮሚቴ ማዋቀሩን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአሁኑ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ጥሪ የትግራይ አመራሮች በድርድሩ የሚሳተፈውን ቡድን እንዲመሩ አቶ ጌታቸው ረዳን እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይን መሰየማቸውን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት እና ኬንያታ

የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ለሦስተኛ ዙር በተቀሰቀሰ በጥቂት ሳምንታት ልዩነት የትግራይ ኃይሎች ተኩስ ቁሞ ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን ባሳወቁበት መግለጫ በአፍሪካ ኅብረት ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸው ቀደም ሲል ይዘውት የነበውን አቋማቸውን እንደቀየሩ አመልክቷል።

የትግራይ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያደራድሯቸው በይፋ ጠይቀው ነበር።

ከቀናት በፊት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል “ዳግም የተከፈተብን” ያሉትን ጥቃት የፀጥታው ምክር ቤት “በኃይል ጣልቃ ገብቶ” እንዲያስቆም በጠየቁበት ደብዳቤ አስተዳደራቸው በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ላይ ጥያቄ እንዳለው አመልክተው ነበር።

በአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ተወካዮች ላይ ያለንን አቋም ከዚህ ቀደም ግልጽ አድርገናል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በተባበሩት መንግሥታት አማካይነት የሚሰየም አደራዳሪ ቡድን አባላት በእኛ ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ አሳስበው ነበር።

በተመሳሳይ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ኅብረት ለኢትዮጵያ ሰላም ሊያመጣ አይችልም የሚል አቋማቸውን በቅርቡ በይፋ አንጸባርቀው ነበር።

ከጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ጋር ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እንዲደራደሩ የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳ 'ዘ አፍሪካ ሪፖርት' ላይ በወጣው ጽሑፋቸው፤ የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኤርትራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ መግባት አለባት ማለታቸውን በማስታወስ የትግራይ አመራሮች ኅብረቱ ለኢትዮጵያ ሰላም ስለማምጣቱ ጥርጥር እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ለሚካሄደው ጦርነት መፍትሔ በመፈለጉ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ቀዳሚው አሸማጋይ ሊሆን እንደሚገባ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

ይህ በሁለቱ ወገኖች በኩል ያለው የአደራዳሪ ፍላጎት ልዩነት ሰላም በማምጣቱ ጥረት ሂደት ላይ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ተብሎ ቆይቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ባለፉት በርካታ ወራት ወደ መቀለ እና አዲስ አበባ በመመላለስ ከተፋላሚ ወገኖች ጋር ውይይት ሲያደርጉ ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ባለፈው አንድ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካዩ ሆነው ያገለገሉትን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆን የውክልና ጊዜያቸው ማራዘሙን አመልክቷል።

የጦርነት ማገርሸት

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች በፌደራሉ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት ሁለት ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

የፌደራሉ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለወራት ተቆጣጥሮ ከቆየ በኋላ ከባድ ጦርነት ተካሂዶ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ነበር።

ሁለተኛው ዙር ጦርነት ከትግራይ ውጪ በሚካሄድበት ጊዜ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ክልሉ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ከወጡ በኋላ ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ተኩስ አቁሞ ነበር።

አሁን ህወሓት ተኩስ ቆሞ ለንግግር ዝግጁ ነኝ ያለው ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ዳግም ተቀስቅሶ በተለያዩ ግንባሮች ከባድ የተባለ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ በሚገለጽበት ወቅት ነው።

ደብረጺዮን (ዶ/ር) ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ በትግራይ ደቡብ ግንባር (ቆቦ)፣ በደቡብ ምዕራብ ግንባር (ሰቆጣ) እና በምዕራብ ግንባር ጭምሮ በሌሎች ስፍራዎች ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።