ባይደን በኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ያሳለፉት ውሳኔ ባለበት እንዲጸና ወሰኑ

ፕሬዝዳንት ባይደን የፈረሙትና በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ዕቀባን ለመጣል የሚያስችለው ትዕዛዝ ባለበት እንዲቀጥል ወሰኑ።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መስከረም 07/2014 ዓ.ም. መፈረማቸው ይታወሳል።

ትዕዛዙ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕቀባ እንዲጣል የሚፈቅድ ነው።

ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት እንዲሁም በአማራ ክልል አስተዳደር እና በህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተገልጾ ነበር።

ይህ ትዕዛዝ ለአንድ ዓመት የሚቆይ በመሆኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ” ያሉት ሕግ አንድ ዓመት ሞልቶት ተግባራዊነቱ ከማብቃቱ በፊት ባለበት እንዲቀጥል ለአገሪቱ ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል።

በአሜሪካ ሕግ መሠረት አንድ “ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ” ድንጋጌ የተቀመጠለት ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ባሉት 90 ቀናት ውስጥ ባለበት እንዲጸና የሚያደርግ ጥያቄ ካልቀረበበት በስተቀር ተግባራዊነቱ ስለሚያበቃ ነው ፕሬዝዳንት ባይደን ደብዳቤውን የጻፉት።

ፕሬዝዳንቱ ለምክር ቤት አፈ ጉባኤዋ በጻፋት ደብዳቤ “ኢትዮጵያን በሚመለከት መስከረም 07/2014 ዓ.ም. የወጣው ፕሬዝዳንታዊው ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ከተቀመጠለት ጊዜ ባሻገርም ተግባራዊ እንዲሆን” መወሰናቸውን ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እና ከእሱ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያን እንዲሁም የሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋትን አደጋ ላይ የጣለ ነው ብሏል ከዋይት ሐውስ የወጣው መልዕክት።

ጨምሮም በተለይ “መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ብሔር ተኮር ጥቃቶችን ጨምሮ ከባድ የመብት ጥሰቶች እና መድፈር እንዲሁም ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች” መፈጸማቸውንና “የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ተስተጓጉሏል”ሲል ገልጿል።

ይህም ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ “ያልተለመደ እና የተለየ” ስጋት ሆኖ በመቀጠሉ “ኢትዮጵያን በሚመለከት የወጣው የብሔራዊ አስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ቁጥር 14046 ባለበት እንዲቀጥል አስፋላጊ ነው ብየ ወስኛለሁ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጽፈዋል።

መስከረም ወር መጀመሪያ 2014 ዓ.ም. ፕሬዝዳንቱ የፈረሙት ትዕዛዝ ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉንም ወገኖች የሚመለከት ሲሆን፣ የተለያዩ ጥሰቶችን የፈጸሙ እና ሰላም እንዳይወርድ እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ ወገኖችን ተጠያቂ ለማድረግ ፕሬዝዳንቱ ለአሜሪካ ግምጃ ቤት አስፈላጊውን ሥልጣን መስጠታቸው ተገልጾ ነበር።

በወቅቱ ፕሬዝዳንት ባይደን “ይህ የፈረምኩት ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትን የሚያራዝሙ፣ ሰብዓዊ ተደራሽነትን የሚያደናቅፉ እንዲሁም የተኩስ አቁሙን የከለከሉ ወይም ተባባሪ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ አዲስ ማዕቀብ ነው” ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጨምረውም አሜሪካ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመደገፍ እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ እነዚህ ማዕቀቦች በኢትዮጵያ ወይም በኤርትራ ሕዝቦች ላይ ያነጣጠሩ እንዳልሆኑ አሳስበው ነበር።

ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም አሜሪካንን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረት የፌደራል ከመንግሥቱን እና ከህወሓት አመራሮች ጋር ለወራት የቆየ ንግግር ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ ሰላም ለማውረድ የሚያስችል ውጤት ማስገኘት አልቻሉም።

በዚህም ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ በነሐሴ ወር አጋማሽ ዳግም ተቀስቅሶ በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ ይነገራል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወቃል።