የትግራይ አመራሮች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑንና በዚህም የሚሳተፉ ተወካዮችን መሰየሙን አስታወቀ።

በአዲስ ዓመት ዕለት ከትግራይ አመራሮች በኩል የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣በአዲሱ ዓመት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ተኩስ የማይሰማበት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችና የሰብአዊ እርዳታ እቀባ የሚያበቃበትቢሆን ፍላጎታቸው መሆኑን ያትታል።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚደረገው ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠርም አስቸኳይና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆም እንደሚስማሙና ይህንንም ተከትሎ በሚካሄድ ድርድር ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በተደጋጋሚ ግጭቱ ለማስቆም በድርድር ለመሳተፍ ሲገልጽ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ከትግራይ አመራሮች በኩል ለቀረበው ሐሳብ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት ዙሪያ የተለያዩ ወገኖች ተፋላሚ ወገኖቹን ለማሸማገል ጥረት ቢያደርጉም፣ እስካሁን ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ውጤት ሳያገኙ ቆይተዋል።

ከአደራዳሪዎች አንጻርም የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት የሽምግልና ሚናውን እንዲጫወት ሲፈልግ፣ የትግራይ ክልል አመራሮች ደግሞ ተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝዳንት አደራዳሪ እንዲሁኑ እንደሚፈልጉ አሳውቀው ነበር።

በተለይ የትግራይ አመራሮች ለወራት መቀለ እና አዲስ አበባ በመመላለስ ጥረት ሲያደርጉ በነበሩት የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ በሆኑት በኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ላይ እምነት እንደሌላቸው ሲገልጹ ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ግን ባለፈው አንድ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካዩ ሆነው ያገለገሉትን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆን የውክልና ጊዜያቸው ማራዘሙን አመልክቷል።

የኅብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በትዊተር ገጻቸው ላይ ቅዳሜ ዕለት እንዳሰፈሩት፣ በኦባሳንጆ ላይ እምነት እንዳላቸውና “በኢትዮጵያና በአካባቢው ሰላምና እርቅ ለማምጣት” ከሁሉም ወገኖች ጋር እንዲሰሩ እንዳበረታቷቸው ገልጸዋል።

የትግራይ አመራሮች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ባመለከቱበት መግለጫ ላይ በኅብረቱ በሚመራው ድርድር ላይ ተአማኒነት ያለው የሰላም ሂደት እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ ጨምረውም በሂደቱ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ያላቸው አሸማጋዮች፣ መተማመንን የሚፈጥሩ ታዛቢዎች እና ምክር እና ድጋፍ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እንዲካተቱ ጠይቀዋል።

ለዚህም በአስቸኳይ ወደ ድርድር የሚገባ ተደራዳሪ ቡድን ማዘጋጀቱን እና ይህም ጌታቸው ረዳ እና ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ያካተተ ቡድን በሚካሄደው ድርድር የትግራይ ወገንን በመወከል እንዲሳተፉ መሰየሙን ገልጿል።

በትግራይ በኩል በድርድሩ ይሳተፋል የተባለውን ቡድን እንደሚመሩ የተገለጹት ሁለቱ ግለሰቦች ቀደም ሲል በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ እንዲሁም ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ትግራይ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የአመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው።

አቶ ጌታቸው ረዳ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በአማካሪነት እንዲሁም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ወደ ትግራይ ከተመለሱ በኋላ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።

ጄነራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ደግሞ ከ20 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩ ሲሆን፣ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል ከድርጅቱ ከተወገዱት መካከል አንዱ ናቸው። ጄኔራሉ ከፖለቲካው ከወጡ በኋላ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የነበረው አለመግባባት እየተካረረ ሲሄድ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወደ ትግራይ የሄዱ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋርና አማራ ክልል ጥቃት በከፈቱበት ጊዜ የትግራይ መከላከያ ኃይል የተባለውን ሠራዊት ከሚመሩት መካከል አንዱ መሆናቸው ተነግሮ ነበር።

ከወራት በፊት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በትግራይ በኩልም በድርድሩ እንደሚሳተፉ ከመግለጽ ውጪ የተደራዳሪዎቻቸውን ማንነት ሳያሳውቁ ቆይተው ነበር።

አሁን ግን በአህጉራዊው ድርጅት አማካኝነት በሚካሄደው ሽምግልና የተደራዳሪዎቻቸውን ማንነት ከመግለጽ ባሻገር በአስቸኳይ ሊደረጉ የሚገባቸው ያሏቸውን ጉዳዮችን በቅደም ተከተል አስቀምጠዋል።

በዚህም መሠረት በሂደቱ በቅድሚያ ግጭት እንዲቆም ከዚያም በድርድር ላይ የተመሰረተ አጠቃላይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና በተከታይነት ደግሞ ለግጭቱ ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሁሉን አካታች ንግግር እንዲደረግ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

ጥቅምት ወር ላይ ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ የሚታወስ ነው።

በጦርነቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ የሚገመት ሲሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ለተረጂነት መዳረጋቸውን የመንግሥታቱ ድርጀት መረጃ ያመለክታል ።

ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ሁለቱም ወገኖች ተኩስ ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ መቀስቀሱ ይታወሳል።

ጦርነቱም በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን የሚከስ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታት ከባድ ውጊያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ በጻፉት ደብዳቤ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሠራዊት መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተባቸውና ድርጅቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀው ነበር።

ሊቀ መንበሩ በደብዳቤያቸው “የሰላም ሂደቱ ፈርሷል” በመንግሥታቱ ድርጅት አማካኝነት ግጭት እንዲቆምና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በባለሙያዎች የተደገፈ ዓለም አቀፍ የአደራዳሪዎች ቡድን እንዲሰየም ጠይቀዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ለሦስተኛ ዙር ካገረሸ በኋላ በደቡብ፣ በምዕራብ እና በሰሜን ትግራይ አካባቢዎች ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው።

ይህንንም ተከትሎ ለጦርነቱ መፍትሔ ለማፈላለግ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ የሾማቸው ማይክ ሐመር ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።