የፊንላንዱ ፖለቲከኛ በፓርላማ ህንጻ ውስጥ ህይወቱ አልፎ ተገኘ

የፊንላንዱ ፖለቲከኛ በመዲናዋ ሄልስንኪ በሚገኘው የፓርላማ ህንጻ ውስጥ ህይወቱ አልፎ ተገኘ።

የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወክሎ የፓርላማ አባል የነበረው የ30 ዓመቱ ኤምሊ ፔልቶኔን የራሱን ህይወት እንዳጠፋ እንደሚታመን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የግለሰቡ አስክሬን በፓርላማው ህንጻ ውስጥ ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12/ 2017 ዓ.ም መገኘቱ ተነግሯል።

የፖለቲከኛው ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት በርካቶችን ያስደነገጠ ሲሆን የተለያየ አቋም ያላቸው ፖለቲከኞች ሃዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

"በጣም የሚወደድ የማህበረሰባችን አባል ነበር። በጣም ይናፍቀናል። በወጣትነቱ ተቀጨ" ሲሉ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ ቡድን ሊቀመንበር ቲቲ ቱፕራይነን በመግለጫቸው አትተዋል።

ፓርላማው በአሁኑ ወቅት ለዕረፍት የተበተነ ቢሆንም ማንኛውም ኦፊሴላዊ የፖለቲካ ስራዎች ለቀናት እንዳይከናወን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትሪ ኦርፖ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖለቲከኛው ኃዘናቸውን ለመግለጽ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ ያዘዙ ሲሆን በባልደረቦቻቸው ዘንድ በጣም ይወደዱ ነበር ማለታቸውን የአገሪቱ ብሄራዊ ጣቢያ ዋይኤልኢ ዘግቧል።

የፓርላማው አፈ ጉባኤ ጁሲ ሃላ አሆ በበኩላቸው ፓለቲከኛው "በተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተከበረ እንዲሁም በጣም ተወዳጅ የስራ ባልደረባ ነበር" ሲሉ በኤከስ ገጻቸው አጋርተዋል።

ፖሊስ ኢዱስኩንታታሎ ወደተሰኘው የፓርላማ ህንጻ የተጠራው ማክሰኞ ዕለት በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 11:06 ሰዓት ላይ ነበር።

ፖሊስ ከፖለቲከኛው ህልፈተ ህይወት ጋር ተያይዞ ምንም አይነት አጠራጣሪ ነገር እንደሌለ አስታውቋል።

የፔልቶነን ሞት የተረጋገጠው ከሶስት ሰዓታት በኋላ በአጭር የፖርላማ መግለጫ ሲሆን ማህበረሰቡ "የቤተሰቦቹ እና የዘመዶቹን ኃዘን ይጋራል" ብሏል።

ፖለቲከኛው የአገሪቱን ደቡባዊ ክልል ኡሲማን ወክሎ የተመረጠው በአውሮፓውያኑ 2023 ሲሆን የፓርላማ አባል ሲሆንም ለመጀመሪያ ጊዜው ነው።

ሆኖም ወደ ፖለቲካ ቀደም ብሎ የገባው ፔልቶኔን ገና በ18 ዓመቱ ነበር ለጃርቬንፓ ከተማ የከተማ ምክር ቤት አባል ሆኖ የተመረጠው።

በ22 ዓመቱ የከተማዋ ቦርድ ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠ ሲሆን ፤ ይህንን ኃላፊነት በዚህ ዕድሜ በመያዝ የመጀመሪያው ሰው እንደሆነም ሚዲያዎች በወቅቱ ተዘግቧል።

ፔልቶኔን ሰኔ ወር ላይ "ወደ ኢንፌክሽን የተቀየረ የኩላሊት ችግር" ስላጋጠመው "በባለፉት ሳምንታት ከብዙ ፓርላማ ስራዎች እርቄያለሁ" ሲል ሰኔ ወር ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ አስፍሮ ነበር።

በዚሁ ልጥፉ ላይ "በሜይላህቲ [በሄልሲንኪ ከተማ ዳርቻ] ውስጥ ህክምና እያደረግኩ ነው፤ ጊዜም ይወስዳል" ብሎ ነበር።

"ከሆስፒታሉ ብወጣም፤ አሁንም የህክምና እረፍት ላይ ነኝ። ሙሉ በሙሉ ከህመሜ በማገገም ላይ አተኩሬያለሁ" ሲል አስፍሮ ነበር።