ኢራን ለሩሲያ ድሮኖች ለመስጠት ማቀዷን አሜሪካ አስጠነቀቀች

የኢራን ድሮኖች

የፎቶው ባለመብት, Iranian Army/Getty Images

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ኢራን በጦርነት ላይ ላለችው ሩሲያ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን (ድሮን) ልትሰጥ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።

ኢራን በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ድጋፏን ለሩሲያ ሰጥታለች። ድጋፏን በተግባር ለማገዝ ማቀዷንም አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

እኒሁ ባለሥልጣን ከፍተኛ የሆነ የውጊ አቅም ያላቸውን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ኢራን ለሩሲያ ልትሰጥ መሆኗን ደርሰንበታል ብለዋል።

የዋይት ሐውስ ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን እንዳሉት ኢራን የሩሲያን ወታደሮች ስለድሮኖች አጠቃቀም ለማሠልጠን ዝግጅት ላይ መሆኗን መረጃ ደርሶናል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ኢራን ድሮኖቹን ለሩሲያ ስለመስጠቷ እስካሁን ግልጽ መረጃ አለመኖሩንም ጠቁመዋል።

ዩክሬን በበኩሏ ባለፈው ሳምንት ጦርነቱን ለማሸነፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እንደሚያስፈልጓት ምዕራባውያንን እርዳታ ጠይቃለች።

ሱሊቫን በመግለጫቸው የኢራን ድሮኖች ከአሁን በፊት ሳዑዲ አረቢያን ለማጥቃት በየመን የሃውቲ አማጺያን አማካኝነት ጥቅም ላይ ውለዋል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ይህንን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዚህ ሳምንት እስራኤል እና ሳዑዲ አረቢያን ለመጎብኘት በዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት ነው።

ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ሁለቱ አገራት ደግሞ አንዳቸውም በሩሲያ ላይ ማዕቀብ አልጣሉም። ከምድረ ገጽ ትጠፋ ስትል የምትዝትባትን ኢራንን እስራኤል የአካባቢው ከፍተኛ ስጋት አድርጋ ትመለከታታለች።

የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በየካቲት ወር ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ እና አጋሮቿ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሣሪያ ድጋፍ ለዩክሬን ለግሰዋል።

አሁንም “ዩክሬን ጥቃቱን በአስተማማኝ ሁኔታ እንድትመክት” እርዳታቸውን እንደሚቀጥሉ የደኅንነት አማካሪው ሱሊቫን ተናግረዋል።