ቢጫው የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ማሊያ እና ፖለቲካን ምን አገኛቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ነሐሴ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ለገበያ ሲቀርብ ጃዎ ቪቶር ወደ ቡቲክ እየበረረ ሄደ።
የ20 ዓመቱ ተማሪ ቅርቡ ካለ አንድ ቡቲክ ገብቶ ቢጫውን ማሊያ ሸመተ። ነገር ግን ባለሱቁ በግልምጫ ገረመመው።
“ባለቡቲኩ አሁን የወቅቱን መንግሥት የምድገፍ መስሎት ግራ ዘመሙን ሉላን ይነቅፈው ጀመር” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጃዎ የቦልሶናሮ መንግሥት ደጋፊ አይደለም። ነገር ግን ያንን ቢጫ ማሊያ ሲገዛ ሰዎች የቦልሶናሮ ደጋፊ አድርገው ሊያስቡት እንደሚችሉ ገመተ።
ቢሆንም ሰዎች ግራ ከሚገባቸው ይሻላል በማለት የቦልሶናሮ ደጋፊ መስሎ ይቀርባቸዋል።
ፔሌ እና ሮናልዶ አልፎም በርካታ ድንቅ ብራዚላዊያን ተጫዋቾች በክብር የለበሱት ቢጫው ማሊያ ብራዚል ውስጥ የፖለቲካ መገለጫ ሆኗል።
በብራዚሊያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ማቴዮስ ጋምባ ቶሬዝ “ይህ ማሊያ ከ2014 ጀምሮ ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው ሆኗል” ይላሉ።
ከስምንት ዓመታት በፊት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ብራዚላዊያን ጎዳና ወጥተው የወቅቱን ፕሬዝዳንት ዲልማ ሩሴፍ ሥልጣን ይልቀቁ ሲሉ ድምፃቸውን አሰሙ።
በወቅቱ ተቃዋሚዎቹ የአገሪቱን ባንዲራ ቀለማትን ለብሰው ነበር ለተቃውሞ የተሰለፉት።
በ2018 ቀኝ ዘመሙ ፖለቲከኛ ጃይር ቦልሶናሮ ይህንን ቀለም መለያቸው አድርገውት በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ታዩ።
አሁን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ሰማያዊ የቦልሶናሮ ካምፕ መለያ ሆኗል። ደጋፊዎችቸው ቢጫ ቲሸርት አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት።
“አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ሰማያዊ አሁን፣ አሁን የቦልሶናሮ ደጋፊዎች መለያ ሆኗል” ይላሉ ቶሬዝ “ይህ ማለት በርካታ ሰዎች ከዚህ ቀለም ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው አይፈልጉም ማለት ነው።”
ጃዎ፤ ልብስ ነጋዴው ማሊያውን አስታኮ ፖለቲካዊ አስተያየት ስለሰጠው ብቻ አይደለም ‘ፖለቲካን እንደ እሣት’ ይሸሽ የጀመረው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አደገኛው የብራዚል ፖለቲካ
ብራዚል ውስጥ ስለፖለቲካዊ አቋም በይፋ መናገር ነብስ ሊያስነጥቅ ይችላል።
ባፈለው ሐምሌ የሉላ ዳ ሲልቫ ደጋፊ የሆነው ማርሴሎ አሎይዚዮ ድ አሩዳ 50ኛ ዓመት ልደቱን እያከበረ ሳለ የቦልሶናሮ ደጋፊ ነኝ ባለ ፖሊስ መገደሉ ይታወሳል።
አሩዳ ከመሞቱ በፊት የተኮሰበት ፖሊስ ላይ ተኩሶ ካቆሰለው በኋላ ነው ያሸለበው።
የፖሊስ መኮንኑ አሁን ከሆስፒታል ወጥቶ ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ ባለፈው መስከረም የ44 ዓመቱ ቤኔዲቶ ካርዶሶ ዶ ሳንቶስ ከሥራ ባልደረባገው ጋር በገባው የፖለቲካ ክርክር ምክንያት መገደሉ ተዘግቧል።
የ22 ዓመቱ ተጠርጣሪ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።
የ43 ዓመቱ የቴክኖሎጂ ፕሮግራመር ሩይ አራውሆ ሱዛ በአሁን ወቅት ይህን የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ማሊያን ቤት ውስጥ ብቻ እንደሚለብሰው ለቢቢሲ ይናገራል።
አራውሆ፤ ምናልባት አሁን ሉላ ሥልጣን ላይ ስላሉ ደማቁ ቢጫ ቀለም እንደቀድሞው ብራዚላዊያንን ያዋህዳል የሚል እምነት አለው።
ግራ ዘመሙ ሉላ የብራዚል ባንዲራ ወደቀደመ ክብሩ እንደሚለስ ይሻሉ።
ከደጋፊዎቻቸው መካከል ታዋቂ አርቲስቶች የብራዚል ባንዲራ ቀለማት ያለበት ቲሸርት ለብሰው መታየት ጀምረዋል።
ከታዋቂ የሉላ ደጋፊዎች መካከል አንዱ የሆነው ራፐሩ ጆንጋ “የቦልሶናሮ ደጋፊዎች ሁሉም ነገር የራሳቸው እንደሆነ ያስባሉ” ሲል ነቀፋ አሰምቶ ነበር።
ነገር ግን የቦልሶናሮ ተቃዋሚዎች ብቻ አይደሉም የብራዚልን ማሊያ ለብሰው ጎዳና ላይ መታየት የሚፈሩት።
“እኔ ቀኝ ዘመም አገር ወዳድ ነኝ። ይህን ማሊያ ለብሼ ድምፄን መስጠት እፈልጋለሁ” ትላለች የቦልሶናሮ ደጋፊዋ አሌሳንድሮ ፓሶስ።
ነገር ግን በአገሪቱ ባለው የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ማሊያውን ለብሳ ወደ ምርጫ ጣቢያ ለመሄድ የሚያስችል ድፍረት የላትም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተጫዋቾች ስለማሊያ ምን ይላሉ?
የብራዚል እና የቶተንሃም አጥቂው ሪቻርልሰን ማሊያው ከፖለቲካ አቋም ጋር መያያዙ ባንዲራው ያቀፈውን አንድነት የሚያወድም ነው ብሎ ያስባል።
“እንደ ደጋፊ፣ ተጫዋች እና ብራዚላዊ፤ እኔ አብሮነትን ማስፋፋት እፈልጋለሁ። እኛ ከሁሉም በላይ ብራዚላውያን መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባል።”
ናይኪ በቅርቡ የብራዚል ማሊያን ሲያስተዋውቅ ከሁለቱም የፖለቲካ ጎራ ያሉ ሰዎችን አሳትፎ፤ አንድነትን ማዕከል ያደረገ መልዕክት ለማስተላለፍ ሞክሯል።
ናይኪ የተሰኘው የስፖርት ዕቃዎች አምራች ማሊያው ከፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መልዕክቶች ጋር ተያይዞ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዷል።
በርካታ ብራዚላውያን ሰማያዊውን ማሊያ መግዛት እየመረጡ ነው። ሰማያዊው ሁለተኛ ማሊያ በተለቀቀ በሰዓታት ውስጥ ተሽጦ አልቋል።
አብዛኛዎቹ የብራዚል የስፖርት ቡድኖች ከቢጫው ማሊያ ይልቅ ሰማያዊውን ማሊያ አርማቸው ማድረግ ጀምረዋል።
ፕሮፌሰር ጋምባ ቶሬዝ ግን ለብራዚላውያን አንድ ምክር አላቸው “ማሊያውን ከፖለቲካ አርቁት” የሚል።
“እርግጥ ነው ማሊያው መልዕክት አለው። ነገር ግን የአንድ የፖለቲካ ጎራ መለያ አይደለም። መንግሥት ይመጣል ይሄዳል። አገራችን እና ብሔራዊ ቡድናችን ግን ሁሌም ይኖራሉ።”












