በአማራ እና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በድርቅ ምክንያት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, WAGHIMRA COMMUNICATIO
በአማራ እና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በድርቅ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ቢሆንም ነዋሪዎች በቂ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆኑ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
በትግራይ ክልል ከአበርገለ አካባቢ በድርቅ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጭላ ከተማ ከሚገኙ ሰዎች መካከል 46 የሚሆኑት በረሃብ መሞታቸውን የክልሉ የአደጋ ሥጋት ኮሚሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ገብረሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በበኩላቸው፣ እስካሁን ከድርቁ ጋር በተያያዘ ቢያንስ የስድስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ4ሺህ በላይ እንስሳት መሞታቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር ገብረሕይወት ገብረ ጨምረው እንዳሉት የእርዳታ አቅርቦት ለሚገባቸው ተጠቃሚዎች ሳይደርስ ስርቆት ተፈጽሞበታል በሚል የምግብ እርዳታ መቋረጡን ተከትሎ በትግራይ ክልል እስከ አሁን 1329 በረሃብ መሞታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል፣ ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በተከሰተው ድርቅ በአሁኑ ወቅት በሰዎች እና በእንስሳት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ቢጨምርም እየቀረበ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን አቶ ምህረት ገልጸዋል።
የሰብአዊ እርዳታ በተቋረጠባቸው በርካታ የትግራይ አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ማጋጠሙ ሌላ ፈተና መሆኑን ዶ/ር ገብረሕይወት ተናግረው፣ ሁኔታው በክልሉ አሁን በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመው ወደ ትምህርት ቤት ይገቡ የነበሩ ልጆችን ተስፋም ያጨለመ ሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል፣ በፌደራል መንግሥት እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ትብብር ወደ 10 ሺህ ኩንታል እህል እንዲገባ መደረጉን እና የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን የገለጹት ኃላፊው፣ በዞኑ ውስጥ ለድርቅ ከተጋለጡ ከ435 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል ድጋፍ ማቅረብ የተቻለው 35 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ብቻ ነው ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ እንደሚሉት በቀረበው እርዳታ የሰዎችን ሞት መግታት የተቻለ ቢሆንም በድርቁ ምክንያት የሚሞቱ እንስሳት ቁጥር ግን እየጨመረ መጥቷል።
በዚህም ምክንያት ከ171 ሺህ በላይ እንስሳት አጎራባች ወደ ሆነው ደሃና ወረዳ ለተወሰነ ጊዜ በጥገኝነት እንዲቆዩ ተደርገዋል።
በድርቅ የተጎዱ እንስሳት ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ የበሽታ መዛመት እንዳይኖር በተቀባይ አካባቢ ላሉትም ሆነ ለሚሰደዱት እንስሳት ክትባት መሰጠት እንዳለበት የገለጹት ኃላፊው፣ የክትባት መድኃኒት እጥረት በማጋጠሙ ሁሉም ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ አለመቻሉንም ኃላፊው ተናግረዋል።
ተማሪዎችም እንስሳቶቻቸውን ተከትለው በመሄድ ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል።
በዞኑ ድርቅ ከተከሰተባቸው ሦስት ወረዳዎች መካከል የከፋ ድርቅ በተከሰተበት ሰሃላ ሰየምት ወረዳ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸውን ከሳምንታት በፊት የዞኑ ኮሚኒኬሽን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ማንነት ተኮር ጥቃቶችን ሸሽተው የወጡትን እንዲሁም ጦርነቱን ተከትሎ የትግራይ አዋሳኝ ከሆነው አበርገሌ ወረዳ የተፈናቀሉትን ጨምሮ ከ23 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።
በዞኑ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተው ድርቅ የሚደርሰውን ጉዳት ለመግታት በክልሉ፣ በፌደራል መንግሥት እና በሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ቢቀርብም በቂ አለመሆኑን እና ሁሉንም ለድርቁ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን መድረስ አለመቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል።
ድርቅ በተከሰተባቸው የአማራ ክልል፣ ዋግ ኽምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ውስጥ ቢያንስ የ40 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የክልሉ አደጋ እና መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን መስከረም 22/2016 ዓ.ም በሰጠው መግለጫም በአማራ ክልል የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ 1 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አስታውቆ፣ የረድኤት ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
በሰሜኑን ጦርነት ወቅት በትግራይ የእርዳታ እህል ላልተገባ ዓላማ ውሏል በሚል የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያቀርቡትን እርዳታ ካቋረጡ በኋላ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ተፈናቃዮችና ስደተኞች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል።
ሆኖም ዩኤስኤአይዲ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ያቀርበው የነበረውና አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ከኅዳር 21/2016 ጀምሮ ዳግም ሊጀምር እንደሆነ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ እና በጦርነት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት መግለጻቸው ይታወቃል።












