ጁቬንቱስ በጣሊያን እግር ኳስ ማኅበር የ15 ነጥብ ቅጣት ተጣለበት

ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጣሊያኑ የእግር ኳስ ቡድን ጁቬንቱስ ከዚህ በፊት ካደረገው የተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ 15 ነጥብ ቅጣት እንደተወሰነበት የአገሪቱ እግር ኳስ ማኅበር አስታወቀ።

የጣሊያን ሴሪ አ ግዙፍ ቡድን የሆነው ጁቬንቱስ ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ የወጪና የገቢ መረጃውን በተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ አቅርቧል ተብሎ ተከሶ ነው የተቀጣው።

በጣሊያን የእግር ኳስ ሊግ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ጁቬንቱስ በቅጣቱ 15 ነጥብ ሲቀነስበት ወደ 10 ደረጃ ላይ ይወርዳል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት አንድሪያ አንጌሊ እና ምክትላቸው ፓቬል ኔድቬድን ጨምሮ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ባለፈው ኅዳር ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል።

ጁቬንቱስ ቅጣቱን ተከትሎ ምንም ጥፋት አልፈጸምኩም በማለት እያስተባባለ ሲሆን ይግባኝ እንደሚጠይቅም አሳውቋል።

በቡድኑ ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተው የእግር ኳስ ማኅበሩ የተጣለው ቅጣት ዐቃቤ ሕጎች ከጠየቁት ጠንከር ያለ ነው። በዚህም በክሱ ላይ የዘጠኝ ነጥቦች ቅጣት ቢጠየቅም የተላለፈው ቅጣት ወደ 15 ነጥቦች ቅነሳ ከፍ ብሏል።

ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ለእንግሊዝ ቡድን ቶተንሃም በሥራ አስኪያጅነት የሚሰራው የቡድኑ የቀድሞ የስፖርት ዳይሬክተር ፋቢዮ ፓራቲሲ ከሁለት ዓመት በላይ እገዳ ተጥሎበታል።

በተጨማሪም በአጠቃላይ 11 የሚሆኑ የጁቬንቱስ የቀድሞ እና የአሁን ከፍተኛ በላሥልጣናትም ከሁለት ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚደርስ እግድ ተላለፎባቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጣሊያን እግር ኳስ ማኅበር ቅጣቱን ከወሰነ በኋላ እንዳስታወቀው ውሳኔው በአውሮፓ ውስጥ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ለአውሮፓ የእግር ኳስ ማኅበር (ዩኤፋ) እና ለፊፋ እንዲያውቁት ይደረጋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ላይ ክሱ በመጀመሪያ ከቀረበ በኋላ ጁቬንቱስ እና ሌሎች 10 ቡድኖች እና 59 ግለሰቦች ላይ የቀረበው ክስ እንዲዘጋ ተወስኖ ነበር።

ነገር ግን የአገሪቱ ፌደራል ዐቃቤ ሕግ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ በመጠየቁ ባለፈው ታኅሣሥ መልሶ በመከፈቱ ነው ጁቬንቱስ ለቅጣት የተዳረገው።

ይህም ቱሪን በሚገኘው ዐቃቤ ሕግ አማካይነት በቡድኑ የገንዘብ ዝውውር ላይ በተደረገው ምርመራ አዳዲስ መረጃዎች በመገኘታቸው ነገሩ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል።

የክስ መዝገቡ መልሶ ተከፍቶ ውሳኔ እንዲሰጥ በተደረገበት ጊዜ ጄቬንቱስ፣ ሳምፕዶሪያ እና ኢምፖሊን ጨምሮ ዘጠኝ ቡድኖች እና 52 የክለቦቹ ሥራ አስፈጻሚዎች ጉዳይ እንዲታይ ተደርጓል።

የጁቬንቱስ ጠበቃ ከውሳኔው በኋላ እንዳሉት የእግር ኳስ ማኅበሩ በቡድኑ ላይ የጣለው ቅጣት “በተመሳሳይ ከተከሰሱት ቡድኖች እና ሥራ አስኪያጆች አንጻር ግልጽ ልዩነት የተደረገበት ከባድ ቅጣት ነው” በማለት ጉዳዩን ወደ ቀጣይ የሕግ አካል በመውሰድ እንዲስተካከል እንደሚያስደርጉ ተናግረዋል።

ጁቬንቱስ አንድሬ አንጌሊ ፕሬዝዳንቱ በነበሩባቸው 13 ዓመታት ውስጥ ለተከታታይ ዘጠኝ ጊዜያት የሴሪ አ አሸናፊ ለመሆን የቻለ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ግን አራተኛ ሆኖ አጠናቋል። በተጨማሪም በጣሊያን ታሪክ ከፍተኛው ነው የተባለው 254 ሚሊዮን ዩሮ ኪሳራም ደርሶበታል።

ባለፈው ረቡዕ የቡድኑ ባለድርሻዎች ባደረጉት ስብስባ የጁቬንቱስ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትን የሰየመ ሲሆን ጂያንሉካ ፌሬሮን ደግሞ ሊቀ መንበር አድርጎ ሾመዋል።

በተጨማሪም ባለፈው ወር የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር በጁቬንቱስ ላይ የተለያዩ ከዝውውር ጋር በተያያዙ ክሶች ዙሪያ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።