ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ለአምስተኛ ጊዜ ተሞሸሩ

የፎቶው ባለመብት, News Corp
የበርካታ ሚዲያ ተቋማት ባለቤት የሆኑት ሩፐርት መርዶክ በካሊፎርኒያ በተከናወነ የሠርግ ስነ-ስርዓት ለአምስተኛ ጊዜ ትዳር መሰረቱ።
የ93 ዓመቱ አዛውንት ሩሲያዊቷን አዲሷ ባለቤታቸው ኤሌና ዝሁኮቫ ጋር ትዳር መስረተዋል።
የፎክስ ኒውስ፣ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዘ ሰን እና ዘ ታይምስ የተባሉ እውቅ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሚዲያዎች ባለቤት የሆኑት መርዶክ፤ 20 ቢሊዮን ገደማ የተጣራ ንብረት እንዳላቸው የፎርብስ ሪፖርት ያሳያል።
መርዶክ ከቀድሞ አጋራቸው አና ስሚዝ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ከአንድ ዓመት በፊት እንዳቋረጡ ከ67 ዓመቷ ሩሲያዊት ጋር የፍቅር ግንኙነት ስለመጀመራቸው ሲገለጽ ነበር።
ሮበርት መርዶክ አዲሷን ሚስታቸውን የተዋወቁት ትውለደ ቻይናዊት የነበረችው የቀድሞ ባለቤታቸው ዌንዲ ዴንግ አዘጋጅታው በነበረ ድግስ ላይ ነው ተብሏል።
ትውለደ አውስራሊያዊው መርዶክ 6 ልጆችን ወልደዋል።
ኤሌና ዝሁኮቫ ከመርዶክ በፊት ከሩሲያዊው ቢሊየነር አሌክሳንደር ዝሁኮቭ ጋር በትዳር አብረው ኖረዋል። ኤሌና ከ አሌክሳንደር የወለዷት ልጃቸው የቀድሞ የቼልሲ እግር ኳስ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ሚስት ነበረች።
እአአ በ1950ዎች ወደ ንግድ ዓለም የገቡት ሩፐርት መርዶክ፤ በ1960ዎቹ በዩናይትድ ኪንግደም ኒውስ ኦፍ ዘ ዎርልድ እና ዘ ሰን የተባሉ ጋዜጠኞችን በመግዛት ነበር የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት መሆን የጀመሩት።
በመቀጠል ኒው ዮርክ ፖስት እና ዎል ስትሪት ጆርናል የተባሉ እውቅ የአሜሪካ ጋዜጦችን ጨምሮ በርካታ የሚዲያ ተቋማትን ገዝተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በተመልካች ብዛት ቁጥር አንድ የሆነውን ፎክስ ኒውስ እአአ 1996 ላይ ከፍተዋል።
መርዶክ ኒውስ ኮርፕ በተሰኘ ኩባንያቸው ስር የሚተዳደሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ መገናኛ ብዙሃንን ያስተዳድራሉ።












