ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኬንያ ፖሊስ ባለፈው አመት 167 ሰዎችን ገድሏል – አምነስቲ
የኬንያ ፖሊስ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ 167 ሰዎችን ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ መግደሉንና አንዳንዶቹም የኮቪድ-19 ክልከላዎችን በመተላለፋቸው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ እንደሆኑ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2021፣ 33 ሰዎች በፖሊስ ተገድደው ተወስደው የት እንዳሉ እንደማይታወቅና ማንም ኃላፊነት እንዳልወሰደ የመብት ተሟጋቹ ገልጿል።
የፈረንጆቹን 2021 በሸፈነው በአምነስቲ ሪፖርት ላይ የኬንያ ፖሊስ ተገቢ ያልሆነና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ፤ አንዳንዴም ለሞት የሚያበቃ ኃይል በመጠቀም ሰልፎችን ለመበተን ሞክሯል ሲል ከሷል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉትና ጥቃት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ክስ እንኳን እንዳልተመሰረተባቸው አስታውቋል።
''በቁጥጥር ስር ውለው መድረሻቸው ካልታወቁትና በሕገወጥ መንገድ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ይፋዊ ክስ የተመሰረተው በ28 ሰዎች ላይ ብቻ ነው'' ብሏል አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ላይ።
በሪፖርቱ ላይ ከተጠቀሱት ግድያዎች መካከል በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በተካሄደው የትራንስፖርት፣ ጤና እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተቆጣጠሪ ተቋም ላይ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ያለአግባብ በፖሊስ ተተኩሶበት የተገደለው አሌክስ ማቻሪያ ዋንጂኩ በዋነኛነት ይጠቀሳል።
''ይህንን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ ገለልተኛው የኬንያ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ተቋም እና ገለልተኛ የሲቪል ተቋም በጥምረት እየሰሩት የነበረው ምርመር እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቀም'' ብሏል አምነስቲ።
ይህንን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት በተመለከተ የኬንያ ፖሊስ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፖሊስ የኮቪድ-19 መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚል ተገቢ ያልሆነ ኃይል በመጠቀሙና ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ላይ ይቅርታ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የኬንያ ፖሊስ በርካታ የጭካኔ ተግባራትን የሚፈጽሙ አባላት እንዳሉበት በተደጋጋሚ ቢገለጽም የፖሊስ ኃላፊዎች ግን የጸጥታ አካላቱ በተገቢው መንገድ ስልጠና የወሰዱ ናቸው ይላል።