አውስትራሊያ ጆኮቪች ቪዛ ስለማግኘቱ ማረጋገጫ አልተሰጠውም አለች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ታዋቂው የቴኒስ ተጫዋች ኖቫክ ጆኮቪች ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የተለየ የጤና ፍቃድ አልተሰጠውም ሲሉ ጆኮቪችን ከአገር ለማስወጣት እየተከራከሩ የሚገኙ ጠበቆች አስታወቁ።
የአውስትራሊያን መንግሥት ወክለው የሚከራከሩት ጠበቆች ለፍርድ ቤት ያስገቡት ሰነድ የ34 ዓመቱ ጆኮቪች የኮቪድ-19 ክትባትን እንዳልተከተበ አሳይተዋል።
በአውስትራሊያ ሕግ መሠረት የተለየ የጤና ፍቃድ እስካልተገኘ ድረስ ቢያንስ ሁለት ጊዜ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ያልወሰደ ሰው ወደ አገሪቱ መግባት አይችልም።
የቴኒስ ተጫዋቹ ከአውስትራሊያ እንዳይባረር ጠበቆቹን አቁሞ እየተከራከረ ነው ይገኛል።
የጆኮቪች የጠበቆች ቡድን እንደሚለው በቅርቡ በቫይረሱ መያዙ በቂ የሆነ የጤና ፈቃድ ያስገኝለታል በማለት ተከራክረዋል። ሰርቢያዊው የቴኒስ ተጫዋች በአውስትራሊያ ኦፕን ውድድር ለመሳተፍ ወደ አውስትራሊያ ያቀናው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።
ነገር ግን ተጫዋቹ በአውስትራሊያ ኢሚግሬሽን ማቆያ ውስጥ እንዲቆይ የተገደደ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ጠበቆቹ የአውስትራሊያ መንግሥት የሰጠውን ቪዛ እንዳይሰርዝበት ለማድረግ እየጣሩ ነው።
የአውስትራሊያ ኦፕን አዘጋጅ ኮሚቴ በበኩሉ ተጫዋቹ በውድድሩ እንደሚሳተፍ እስከ ማክሰኞ ድረስ እንዲያስታውቅ ጠይቋል። ጆኮቪች የሚሳተፍበት ውድድር በፈረንጆቹ ጥር 9 ነው የሚጀምረው።
ባሳለፍነው ቅዳሜ የጆኮቪች ጠበቆች ባለ 35 ገጽ ሰነድ ለአውስትራሊያ መንግሥት ያስገቡ ሲሆን ተጫዋቹ በቅርቡ በኮሮናቫእረስ መያዙ ክትባት ሳይወስድ ወደ አገሪቱ እንዲገባ የሚያስችለው ፍቃድ ነው ብለው ተከራክረዋል።
ተጫዋቹ ባሳለፍነው ወር አጋማሽ ላይ በቫይረሱ ተይዞ ነበር።
ነገር ግን ትናንት እሁድ በነበረው የፍርድ ቤት ሂደት የአውስትራሊያ መንግሥት ጠበቆች ይህንን ምክንያት ውድቅ አድርገውታል።
"ተጫዋቹ ከበድ ያለ ህመም አስተናግዶ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አልቀረበም። በኮቪድ-19 ተይዞ እንደነበር ብቻ ነው የሚገልጸው። ይህ ደግሞ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት የተቀመጠውን ሕግ ሙሉ በሙሉ አያሟላም'' ሲሉ ተከራክረዋል።
ጆኮቪች ከዚህ በፊት በክትባት እንደማያምን ተናግሮ የነበረ ሲሆን ነገር ግን እስካሁን በይፋ ክትባቱን ይውሰድ አይውሰድ የገለጸው ነገር የለም።
ጆኮቪች ወደ አውስትራሊያ ለመግባት ልዩ የጤና ማረጋገጫ ተሰጥቶታል የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ ለበርካታ ወራት በጥብቅ የኮቪድ መመሪያዎች ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ አውስትራሊያውያን ቁጣቸውን ገልጸዋል።












