በካዛኪስታን የፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች በትንሹ 164 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጤና ባለስልጣናትን በመጥቀስ በተሠራ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሠረት በካዛኪስታን የተቀሰቀሰው የፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎችን ተከትሎ ቢያንስ 164 ሰዎች ተገድለዋል።
ቁጥሩ ከተረጋገጠ ቀደም ሲል ከነበረው የ44 ሰዎች ሞት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ያመላክታል።
የካዛኪስታን ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት እሑድ ዕለት እንዳስታወቀው "በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ" ወደ 6,000 የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል።
በነዳጅ ዋጋ ንረት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ተባብሶ በመላ ሃገሪቱ ተስፋፍቷል። ከሳምንት በፊት በተጀመረው ተቃውሞ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለውን ቅሬታ እየገለጸ።
ሕግ ለማስከበር ባለፈው ሳምንት የሩሲያን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ወታደሮች በአገሪቱ ፕሬዝደንት ጋባዥነት ወደ ካዛክስታን አቅንተዋል።
ፕሬዚዳንቱ በትናንትነው መግለጫቸው ሁኔታው መረጋጋቱን ጠቅሰው ወታደሮች "የማጽዳት" ሥራዎችን መቀጠላቸውን እና "ወሳኝ ተቋማትን" በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ እንደቀጠለ ነው።
በዋና ከተማዋ ኑርሱልጣን የፀጥታ ጥበቃው መጠነከሩን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ነው ያለው የቢቢሲው ጋዜጠኛ ስቲቭ ሮዘንበርግ ነው።
የተፈጠረው ሁከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በካዛኪስታን ባለስልጣናት መካከል ካለው የስልጣን ሽኩቻ ጋር የተያያዘ ነው ሲል ዘጋቢው አክሎ ገልጿል።
በአልማቲ ከተማ በተፈጠረ ሁከት 103 ያህል ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
የጸጥታ ኃይሎች በአልማቲ ከተማ ሁከት ፈጣሪዎችን የገደሉት ጸጥታ ለማስፈን ሲሞክሩ መሆኑን አስታውቀው ሰልፈኞች በከተማዋ የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር ሞክረዋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቃሲም-ጆማርት ቶካዬቭ በበኩላቸው "20 ሺህ ሽፍቶች" አልማቲ ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው የጸጥታ ኃይሎችን "ያለ ማስጠንቀቂያ ተኩሱ" ማለታቸውን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እሑድ ዕለት የፕሬዚዳንቱን መመሪያ ተችተዋል። "ተኩሶ የመግደል ትዕዛዙ ስህተት በመሆኑ መሰረዝ አለበት" ሲሉ ለኢቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
የሩስያ ወታደሮች በአገሪቱ እንዲገኙ የጠየቁበትን ምክንያት የካዛኪስታኑ ፕሬዝዳንት እንዲያብራሩ አሜሪካ እንደምትፈልግም ገልጸዋል።












