ፖለቲከኞች በአዲሱ ዓመት ሰላም እንዲያሰፍኑ 24 የሲቪል ማኅበራት ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, CARD
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች ምክንያት እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ አሳስቦናል ያሉ 24 አገር በቀል የሲቪል ማኅበራት በግጭቶቹ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው አካላት በአዲሱ ዓመት ሰላም እንዲያወርዱ ጠየቁ።
አስር ነጥቦች ባለው በዚሁ ጥሪያቸው፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ቀውሶቹ በውይይት እንዲፈቱ የተደረጉ ጥረቶች እስካሁን ድረስ መፍትሔ አለማምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ሴቶች ማኅበር፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ ሴታዊት ንቅናቄ፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ ኢኒሺዬቲቭ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት እና የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ከተቋማቱ ውስጥ ይገኙበታል።
"ጦርነት እና ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ደኅንነት ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ለከፍተኛ አደጋ መጋለጣቸው አሳስቦናል" ሲሉ ተቋማቱ ገልጸዋል።
እንዲሁም ለጦርነት መንስኤ የሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ችግሮች በጦርነት በዘላቂነት ሊፈቱ አይችሉም የሚል እምነት አለን ያሉት የሲቪል ተቋማቱ፤ በጦርነት ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ዋናው ዋጋ ከፋይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩትን ከቀያቸው አፈናቅሎ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ለረሃብ አደጋ አጋልጧል።
ይህ ጦርነት በተለይም በወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ እያስከተለ ያለው እልቂት፣ የምጣኔ ሀብት ውድመት እንዲሁም የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በዓለም አቀፍ ሕጎች የተወገዘ ብሎም በአገሪቷ መጻኢ እድል ላይ መጠነ ሰፊ ጫና የሚያስከትል ሆኖ እንዳገኙት ማኅበራቱ ገልጸዋል።
የዚህ ጦርነት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎች ከአገር አቀፍ ጉዳት አልፎ ወደ ቀጠናዊ ቀውስ ሊያመራ የሚችልበት እድል በመኖሩ እንዲሁም ጦርነቱ በመሠረተ ልማቶች ውድመት በማስከተል ኢትዮጵያን ወደ ከፋ ድህነት የሚጎትት ሆኖ በማግኘታቸው የሰላም ጥሪ እንዳደረጉ አስታውቀዋል።
ከምጣኔ ሀብታዊ ብሎም ከፖለቲካዊ ኪሳራዎች ባሻገር ይህ ጦርነት በማኅበራዊ ግንኙነት ላይ እያስከተለ የመጣው ጫና አሳሰቢ ነው ያሉት ተቋማቱ፤ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ፣ በሶማሊ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶችም እንዳሳሰቧቸው ተናግረዋል።
"ሕፃናት ልጆቻችን፣ በዕድሜ የገፉ ወገኖቻችን እና ሴቶቻችን በተለየ ሁኔታ ለመከራ ተጋላጭ እየሆኑ፣ ጾታዊ ጥቃትንና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶች ሰለባ በመሆን ላይ ናቸው" ሲል ጥሪው ያስነብባል።
"ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የምንጠቀምባቸው የሽምግልና እና የዕርቅ ባህላዊና ማኅበራዊ አቅሞቻችንን ለመጠቀም እያደረግን ያለነው ሁለገብ ጥረት እስካሁን ሰላምን ሊያረጋጋጥልን አልቻለም። በመሆኑም ሕዝባችንን ለዘመናት ደግፈው ያቆዩ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ሳይቀሩ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ" ሲሉም ማኅበራቱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ የፖለቲካ ብሎም የጦር ኃይሎች በመጪው ዓመት ቆም ብሎ በማሰብ የሰላም አማራጭን እንዲመርጡ ጠይቀዋል።












