ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንድ ሮኬት ብዙ ሳተላይት ወደ ሕዋ የመላክ ክብረ ወሰን ተሰበረ
በአንድ ጊዜ በአንድ መንኮራኩር ወደ ህዋ የሚላኩ የሳተላይቶች ብዛት ክብረ ወሰን ተሻሻለ፡፡
የተለያዩ ቅርጽና መጠን ያላቸው 143 ሳተላይቶች በአንድ ሮኬት ተጭነው ከፍሎሪዳ ወደ ህዋ ተመንጥቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ በአንድ ሮኬት ብዙ ሳተላይት ተልኮ የነበረው በፈረንጆቹ 2017 ሲሆን የሳተላይቶቹ ብዛትም 104 ብቻ ነበር፡፡
ያን ጊዜ ሳተላይቶቹን ያሳፈረው መንኩራኮር ሕንድ ሠራሽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አሁን ክብረ ወሰኑን የሰበረው የዓለም ቁጥር 1 ቢሊየነር ኤለን መስክ ኩባንያ የፈጠረው ስፔስኤክስ- ፋልከን ነው፡፡
ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሳተላይቶች በአንድ ጊዜ መላክ መቻሉ ቀስ በቀስ የአሠራርና የቴክኖሎጂ አብዮት እየተደረገ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡
ይህም ማለት አንድን ሳተላይት በመጠኑ አሳንሶ፣ በሥራ ቅልጥፍና አዘምኖ በትንንሽ ግብአቶች አምርቶ ወደ ህዋ ማሳፈር መቻሉ ነው፡፡
አሁን አሁን ማንም ኩባንያ ልክ የእጅ ስልክ ማምረት እንደሚችለው ሳተላይቶችን ማምረት የሚችልበት አቅም መፈጠሩን ያስመሰከረ ነው ብለውታል ባለሙያዎች፡፡
አዲሱ የህዋ ታክሲ ስፔስኤክስ (SpaceX) እነዚህ ቀላል ሳተላይቶችን ወደ ኦርቢት ለመላክ ከ1 ሚሊዮን ዶላር ባነሰ ዋጋ መጠየቁ ወደፊት ዘርፉ ለትንንሽ ኩባንያዎች እየተከፈተ እንደሚመጣ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ስፔስኤክስ የራሱ የሆኑ 10 ሳተላይቶች ያሉት ሲሆን በዓለም ዙርያ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ግንኙነቶችን መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡
በዚህ ክብረ ወሰንን በሰበረው የሮኬት ጉዞ የሳንፍራንሲስኮው ፕላኔት የተባለ ኩባንያ 48 ሳተላይቶችን በመላክ ከፍተኛውን የሳተላይት ቁጥር አስመዝግቧል፡፡
እነዚህ የፕላኔት ኩባንያ ንብረት የሆኑ ሳተላይቶች ‹ሱፕርዶቭ› ሞዴል የሚባሉ ሲሆን የመሬትን ገጽታ በየቀኑ በከፍተኛ ጥራት ፎቶ የሚያነሱ ናቸው፡፡
አሁን የላካቸውን 48 ሳተላይቶች ጨምሮ ይህ የሳንፍራንሲስኮው ፕላኔት ኩባንያ በህዋ የሚኖሩት የሳተላይቶች ቁጥር ወደ 200 የሚያደርሰው ይሆናል፡፡
ሱፐርዶቭስ የሚባሉት እነዚህ ሳተላይቶች መጠናቸው የሊስትሮ ሳጥን ቢያክል ነው፡፡ ሌሎቹ በፋልከን ሮኬት የተጫኑት ደግሞ ከአንድ የሻይ ኩባያ መጠን ብዙም የሚበልጡ አይደሉም፡፡
አሁን አሁን ቴክኖሎጂው እየተረቃቀ ሲመጣ የሳተላይቶች ተግባር ሳይቀንስ፣ ነገር ግን መጠናቸው እጅግ እያነሰ ሄዶ ‹ስፔስቢስ› የሚባሉ ‹የህዋ-ንብ› ሊባሉ የሚችሉ ትንንሽ ሳተላይቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡
የነዚህ ሳተላይቶች ጠቅላላ መጠን 10 ሴንቲ ሜትር በ10 ሴንቲሜትር ብቻ ቢሆን ነው፡፡
እነዚህ ‹ስፔስቢስ› የሚባሉት የሳተላይት ጉጦች ሳተላይትን መሬት ላይ ካለ ማንኛውም ቁስ ጋር የማገናኘት ተግባር ይሰጣሉ፡፡
ለምሳሌ ከአገር አገር እየበረሩ ያሉ አእዋፋት ወይም እንሰሳት ወይም ደግሞ መርከቦች ወይም ሌላ ቁስን ህዋ ላይ ካለ ሳተላይት ጋር የሚያገናኙ የሳተላይት ጉጦች ናቸው፡፡
በዚች የስፔስኤክስ ፋልከን መንኮራኩር ትልልቅ ሳተላይቶች የተጫኑ ሲሆን እነዚህ በመጠን ትልቅ የተባሉት ግን አንድ የሳምሶናይት የእጅ ሻንጣ ቢያክሉ ነው፡፡ ብዙዎቹ የራዳር ሳተላይቶች ናቸው፡፡
በተለምዶ የራዳር ሳተላይቶች እጅግ ግዙፍና ብዙ ቶን የሚመዝኑ ሲሆን ወደ ህዋ ለመላክ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ያስፈልጉ ነበር፡፡
ይህም ማለት እነዚህን የራዳር ሳተላይቶች በፊት ግዙፍ የወታደር ተቋም ወይም የስፔስ ኤጀንሲዎች ካልሆኑ ማንም የሚደፍራቸው አልነበሩም፡፡
አሁን አሁን ግን ቴክኖሎጂዎች መራቀቃቸውን ተከትሎ በሚደንቅ ሁኔታ ክብደታቸው ከ100 ኪሎ ግራም እያነሰ ወደ ህዋ ማሳፈርያ ዋጋቸውም ከ2 ሚሊዮን ዶላር ሳይበልጥ ማሳካት ተችሏል፡፡
በትናንቱ የህዋ ጉዞ አይሲየ (Iceye) ከፊንንላንድ፣ አምብራ (Umbra) ከአሜሪካ፣ አይኦፒኤስ (iQPS) ከጃፓን ሳተላይቶችን ልከዋል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች ለዘርፉ ገና ጀማሪዎች ናቸው፡፡ ሳተላይቶቻቸው የመሬትን ምሥል በተከታታይ ይልኩላቸዋል፡፡
ራዳር ከኦፕቲካል ካሜራዎች በተለየ ደመናን ጥሶ በማለፍ የመሬትን ከባቢና ወለል በተሸለ ጥራት ፎቶ የማንሳት አቅም አለው፡፡ በቀን እና ብራ የአየር ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በድቅድቅ ጨለማም ምሥል ማንሳት ይችላል፡፡
ይህም ማለት ምድር ላይ የምትፈጸም አንዳች እንቅስቃሴ በቀላሉ የምትታይበት ዘመን እየመጣ እንደሆነ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡