የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት በኮቪድ ተያዙ

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ኮቪድ ተመርምረው ተህዋሲው እንደተገኘባቸው ይፋ አደረጉ።

የ67 ዓመቱ ፕሬዝዳንት በትዊተር ሰሌዳቸው እንደጻፉት አሁን የበሽታውን ቀላል ምልክቶችን ማሳየት ጀምረዋል።

የፕሬዝዳንቱ በተህዋሲው የመያዝ ዜና የመጣው ሜክሲኮ በወረርሽኝ እየታመሰች ባለችበት ወቅት ነው።

ሜክሲኮ እስከዛሬ ከ150ሺህ ባላይ ዜጎቿን በተህዋሲው አጥታለች።

ሎፔዝ ኦብራዶር አገሪቱን ከቤቴ ሆኜ መምራቴን እቀጥላለሁ ብለዋል። ሩሲያ ሰራሹን ክትባት ለማግኘትም ከፑቲን ጋር እነጋገራለሁ ብለዋል።

ትናንት ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ሰኞ በስልክ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ዙርያ ይነጋገራሉ የሚሉ ዘገባዎች ወጥተው ነበር። ዋናው አጀንዳ የሚሆነውም ሰፑትኒክ የተሰኘውን ሩሲያ ሰራሽ ክትባት ሜክሲኮ የምታገኝበትን ዘዴ መቀየስ ነው።

ባለፈው ዓመት ፕሬዝደንት ሎፔዝ ሩሲያ ሰራሹን የኮቪድ ክትባት ፈዋሽነቱ እንደተረጋገጠ 12 ሚሊዮን ጠብታ ወደ አገሬ አስገባለሁ ብለው ተናግረው ነበር።

ሜክሲኮ ሩሲያ ሰራሹን ክትባት ፈዋሽነት ለጊዜው አላረጋገጠችም። ሆኖም ግን 128 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕዝቧ ክትባቱን ለማዳረስ የፋይዘር ባዮንቴክ መዘግየት ታክሎበት ወደ ሩሲያ ለማማተር ተገዳለች።

አሁን ለሩሲያው ስፑትኪን ክትባት አውቅና የሰጡ ዋና ዋና አገራት ብራዚል፣ አርጀንቲናና ሀንጋሪ ናቸው።

ጆስ ሉዊስ አሎሚያ ዛጋራ የተባለ አንድ የጤና ረዳት የፕሬዝዳንቱን ጤንነት ከገመገመ በኋላ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤ የሚያሳስብ ነገር የለም ብሏል። የጤና ባለሙያዎች ቡድን ለፕሬዝዳንቱ የቅርብ ክትትል እያደረጉላቸው ይገኛሉ።

ሜክሲኮ በተህዋሲው የተያዙባት ዜጎች ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን እየተጠጋ ይገኛል። በ150ሺ ሟቾች ቁጥርም ግማሽ ሚሊዮን እየተጠጋ ያለ ሕዝብ ከሞተባት አሜሪካ፣ እንዲሁም ከብራዚልና ሕንድ ቀጥሎ ከዓለም በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።