እስራኤል የማትሪክ ፈተና ለሚቀመጡ ተማሪዎቿ ክትባት መስጠት ጀመረች

እስራኤል ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 18 የሚሆኑ ወጣቶችን ኮቪድ ክትባት መስጠት ጀመረች።

ለነዚህ ወጣቶች ክትባቱ እንዲሰጠት የሆነው የማትሪክ ፈተና ሊቀመጡ ስለሆነ ነው።

እስራኤል 9 ሚሊዮን ከሚሆነው ሕዝቧ ውስጥ ሩብ ያህሉ የመጀመርያውን የክትባት ጠብታ ወስዷል። የክትባቱ አይነትም ፋይዘር ሰራሹ መሆኑ ታውቋል።

እስራኤል ለዜጎቿ ክትባት መስጠት የጀመረችው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ አካባቢ ከዲሴምበር 19 ጀምሮ ነው።

ክትባቱ ሲጀመር ቅድሚያ የተሰጣቸው እድሜያቸው ለገፉ አዛውንቶች ሲሆን ከዚያም ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ነበር። አሁን ዕድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ዜጎች ክትባቱን በመወሰድ ላይ ናቸው።

እስራኤል ኢኮኖሚዋን በየካቲት ወር ሙሉ በሙሉ ለመክፈት እየታተረች ነው።

የእስራኤል የትምህርት ሚኒስትር እንዳሉት አሁን ወጣት ተማሪዎችን መከተብ የተጀመረው ወደ ትምህርት እንዲመለሱና ፈተና እንዲቀመጡ ለማስቻል ነው።

ወጣት ተማሪዎቹ ክትባቱን የሚወስዱት በወላጆቻቸው ፈቃድ ነው።

እስራኤል ያሉ ተማሪዎች የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሲጨርሱ የሚወስዱት የማትሪክ ፈተና ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት አለመግባት የሚለዩበት ነው።

የሚያመጡት ውጤትም በውትድርና ተሳትፏቸው ላይ ወሳኝ ሚና አለው። በእስራኤል ዜጎች ለተወሰነ ጊዜ የግዴታ የውትድርና አገልግሎትን ይሰጣሉ።

የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ክትባቱ መሰጠቱን እየቀጠለ ቢሆንም በሚቀጥለው ወር ትምህርት ስለመጀመር አለመጀመሩ ለመናገር ጊዜው ገና ነው።

እስራኤል ክትባት በመስጠት ከአለም ፈጣኗ አገር ሆና ነው በዲሴምበር 19 የጀመረችው። በፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ የሕዝቧን 10 እጅ ከትባ ጨርሳለች።

እስራኤል 600ሺህ በተህዋሲው የተያዙ ዜጎች ያሏት ሲሆን 4ሺ የሚሆኑት ሞተውባታል።

ትናንት የእሰራኤል መንግሥት ባወጣው አዲስ መመርያ የመንገደኞች በረራን ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ የጥር ወርን ሙሉ ማገዱን አስታውቋል። ይህም ተህዋሲውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት አንድ አካል ነው።

ቤንያሚን ኔትንያሁ እንደተናገሩት ይህ የበረራ እገድ አዲሱ የኮቪድ ዝርያ ወደ እስራኤል እንዳይገባ ለማድረግ የሚወሰድ ጥብቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የውጭ ዜጎች ወደ እስራኤል እንዲገቡ እየተፈቀደላቸው አይደለም።

እስራኤል በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ 9 ሚሊዮን ዜጎቿን ጸረ ኮቪድ ክትባት በመከተብ የዓለም የመጀመርያዋ አገር ለመሆን ቀን ተሌት እየሰራች ትገኛለች።