ኮሮናቫይረስ፡ ኒውዚላንድ ከወራት በኋላ በቫይረሱ የተያዘች ሴት አገኘች

ከሁለት ወራት በላይ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት ያልታየባት ኒውዚላንድ ከሰሞኑ በቫይረሱ የተያዘች ሴት አግኝታለች።

የጤና ባለሙያዎች ከሰሞኑ ከአውሮፓ የተመለሰች የ56 አመት ሴት ቫይረሱ ተገኝቶባታል።

ግለሰቧ ከሌላ አገራት ለሚመጡ አስገዳጅ የሆነውን የሁለት ሳምንት ለይቶ ማቆያ ጊዜ ጨርሳ ቤቷ ከሄደች ከቀናት በኋላ ነው ቫይረሱ እንደተገኘባት የታወቀው።

ከሴትዮዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸውን እንዲሁም የጎበኘቻቸውን ስፍራዎች ዝርዝር ባለስልጣናቱ እየተከታተሉ ነው ተብሏል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመግታት ዘርፍ ከፍተኛ ሙገሳና ምስጋና ካተረፉ አገራት መካከል ኒውዚላንድ በዋናነት ትጠቀሳለች።

አምስት ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ኒውዚላንድ እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የመዘገበችው ቁጥር 1 ሺህ 927 ሲሆን 25 ዜጎቿም ሞተዋል።

ግለሰቧ በኦክላንድ የነበራትን የለይቶ ማቆያ ጊዜዋን ከጨረሰች በኋላ ባደረገችው ምርመራ ሁለት ጊዜ ከቫይረሱ ነፃ ነሽ ተብላ ነበር።

ከሁለት ቀናት በኋላ ቀለል ያሉ የቫይረሱን ምልክቶች ማሳየት የጀመረች ሲሆን በኋላም እየከፋና እየባሰባት መጥቷል ተብሏል።

ምርመራ ባደረገችበት ወቅት በቫይረሱ እንደተያዘች የታወቀ ሲሆን ከዚያ ቀን በኋላ በቤቷ ራሷን ለይታ ተቀምጣለች።

በዛሬው ዕለት የጤና ሚኒስትሩ ክሪስ ሂፕኪንስ እንዳሉት የቫይረሱ ዝርያ ከየት እንደመጣ ለመገመት በአሁኑ ሰዓት ከባድ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ " የቫይረሱ ዝርያ አይነት በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ እንደሆነ በማሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እያደረግን ነው" ብሏል።

ከዚህ በላይ ግን ስለ ቫይረሱ ምንም ማለት እንደማይቻል ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የለይቶ ማቆያ ጊዜዋን ከጨረሰች በኋላ በሰሜናዊ ኒውዚላንድ የሚገኙ ቦታዎችን ጎብኝታለች ተብሏል።

የጤና ሚኒስቴር ጎብኝታቸዋለች ብሎ የጠቀሳቸውን ሱፐር ማርኬቶች፣ ሬስቶራንቶችና ጋለሪዎች ዝርዝር አውጥቷል።።

በነዚህ በተጠቀሱት ቦታዎች ድንገት ተገኝቶ የነበረ ሰው በሙሉ በጥርጣሬ እንደሚታይና ቤታቸውም ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩና እንዲመረመሩም ተነግሯቸዋል።

ከሴትዮዋ ጋር ቅርበት አላቸው የተባሉ አራት ሰዎች የተለዩ ሲሆን ምርመራ ተደርጎላቸዋል ተብሏል።