ኮሮናቫይረስ፡ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጥን ያበረታቱት የሲሪሊንካ ሚኒስትር በቫይረሱ ተያዙ

ከዕፅዋት የተሰራ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጥን አገራቸው እድትጠቀም ያበረታቱት የሲሪላንካ የጤና ሚኒስትር በቫይረሱ ተያዙ።

የጤና ሚኒስትሯ ፓቪትራ ዋኒያራቺቺ በዚህ ሳምንት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የመስሪያ ቤታቸው ሚዲያ ዘርፍ ፀሐፊ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

የአገሪቱ የባህል ህክምና አዋቂ ለህይወት ዘመን የሚሆን የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጥ ማምረታቸውን ተከትሎ ሚኒስትሯም አገራቸው እንድትጠቀም ሲያበረታቱ ነበር።

ፓቪትራ ዋኒያራቺቺ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጡን በይፋ ሲጠጡም ታይተዋል።

ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ በሲሪሊንካ 56 ሺህ 76 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 276 ዜጎቿንም አጥታለች።

በቅርብ ወራትም በከፍተኛ ሁኔታ እያገረሸ ነው ተብሏል። የጤና ሚኒስትሯ በኮሮቫይረስ የተያዙ አራተኛ ሚኒስትር ሆነዋል።

የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጡ ማርና ገውዝን ጨምሮ ከሌሎች ንጥረ ነገሮች የተቀመመ ሲሆን ውህዱም በህልም እንደተሰጣቸው የባህል ሃኪሙ ተናግረዋል።

የአገሪቱ የጤና ባለሙያዎች የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያው ፍቱንነት አልተረጋገጠም ቢሉም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የባህል ሃኪሙ ወደሚገኝበት መንደር ይጎርፉ ነበር ተብሏል።

የጤና ሚኒስትሯ ሁለት የኮቪድ-19 ምርመራ ቢያደርጉም ሁለቱም በቫይረሱ መያዛቸውን እንደሚያሳይ የሚዲያ ፀሃፊው ቪራጅ አብይሲንጌ ተናግሯል።

ሚኒስትሯ ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩና የቅርብ ቤተሰባቸውም እንዲሁ ራሳቸውን እንዲያገሉ ተጠይቀዋል።

ሲሪላንካ ለድንገተኛ ጊዜ የሚሆነውን የኦክስፎርዱን አስትራዜኔካ ክትባት ዜጎቿ እንዲከተቡ ፈቃድ ሰጥታለች። የመጀመሪያ ዙር ክትባት በሚቀጥለው ወር ይደርሳል ተብሏል።

ፍቱንነቱ ያልተረጋገጠ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ መጠጥ የአንድ አገር ባለስልጣን ሲያበራታቱ እሳቸው የመጀመሪያ አይደሉም።

ባለፈው አመት የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆሊና ከዕፅዋት የተቀመመ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያ ተገኝቷል ማለታቸው ከፍተኛ ትችትን እንዲያስተናግዱ አድርገዋቸዋል። በመዲናዋ መጠጡን ሲያከፋፍሉ ታይተዋል።

ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ የአለም መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና ባለስልጣናት በቫይረሱ ተይዘዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና ዶናልድ ትራምፕ በቫይረሱ ተይዘው ማገገማቸው ይታወሳል።