ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ቻይና አሜሪካንን በልጣ ከዓለም 1ኛ ሆነች
ቻይና በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት (FDI) ለመጀመርያ ጊዜ አሜሪካንን በመብለጥ የምድራችን ቁጥር አንድ አገር ለመሆን በቃች።
ትናንት እሑድ ይፋ በተደረገ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት መሠረት ቻይና አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ይሆናል ተብሎ ከተገመተው በአጭር የጊዜ ሂደት አሜሪካንን ለመብለጥ ችላለች።
ይህ የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ እንደሚያትተው ወደ ቻይና ድርጅቶች አዳዲስ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ4 ከመቶ ተመንድጓል።
በሌላ አነጋገር በፈረንጆቹ 2020 ወደ ቻይና የተመሙ አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ወደ አሜሪካ ከተመሙት አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች በእጅጉ ያላቁ ናቸው።
ይህ የሚያሳየው ቻይና በዓለም ዙርያ ያላት ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ነው ብሏል ሪፖርቱ።
ከውጭ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ አዳዲስ የቀጥታ ኢንቨስትመንቶች ባለፈው ዓመት (2020) በግማሽ መቀነሳቸውን ዘገባው አትቷል።
ሆኖም ወደ ቻይና የሚተሙ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ከዕለት ዕለት እየጨመሩ ነው የመጡት። በዚህም ምክንያት ነው ቻይና ከአሜሪካ ልቃ እንድትገኝ ያስቻላት።
ቻይና ባለፈው ዓመት ብቻ 163 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገሯ አዲስ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈሶላታል።
አሜሪካ ግን 134 ቢሊዮን ብቻ ነው ወደ አገሯ የቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ የቻለችው።
ይህን አሐዛዊ ዘገባ ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በንግድና በልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) ላይ ነው።
በ እአአ 2019 አሜሪካ የ251 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ችላ ነበር። በዚህ ጊዜ ቻይና የ140 ቢሊዮን የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ነበር ማግኘት የቻለችው።
ምንም እንኳ ቻይና በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት አዲስ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ አሜሪካንን ቀድማ አንደኛ ብትሆንም በጠቅላላ የውጭ ኢንቨስትመንት ክምችት ግን አሁንም ዓለምን የምትመራው አሜሪካ ናት።
ይህም የሚያሳየው ለዓመታት አሜሪካ የአዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶች መዳረሻ ተመራጭ አገር እንደነበረችና የውጭ ኢንቨስትምነት ምን ያህል የተከማቸባት አገር መሆኗን ነው ይላል ሪፖርቱ።
የምጣኔ ሀብት አዋቂዎች ግን በአዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የታየው የአሰላለፍ ልዩነት አሁን ቻይና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ የሆነ ተጽእኖ ማሳረፍ መጀመሯን አመላካች ነው ይላሉ።
በአሜሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ2016 የትራምፕን መምጣት ተከትሎ ነበር ወደ 472 ቢሊዮን ዶላር የተመነደገው።
ያን ጊዜ ቻይና 134 ቢሊዮን ዶላር ላይ ነበረች።
ያን ጊዜ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ኩባንያዎች ቶሎ ቻይናን እየለቀቁ ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ ከፍተኛ ማበረታቻ እየሰጠ ነበር።
በተመሳሳይ የትራምፕ አስተዳደር የቻይና ኩባንያዎች ለደኅንነት ስጋት ስለሚሆኑ በየጊዜው ይመረመራሉ በሚል በአሜሪካ የነበራቸው ሚና ለማንኳሰስ ሞክሯል።
ይህ የትራምፕ አስተዳደር በዚህ መንገድ ተጽእኖ ለመፍጠር በመቻሉ ሊሆን ይችላል ባለፉት ዓመታት የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የበላይነት በአሜሪካ ተይዞ የቆየው።
ሆኖም ባለፈው ዓመት (2020) የአሜሪካ ኢኮኖሚ በኮቪድ ወረርሸኝ የተነሳ ሲቀዛቀዝ የቻይና ኢኮኖሚ ግን ቶሎ ማንሰራራት ችሏል።
በ2020 የቻይና የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት መጠን (GDP) በ2.3% ማደጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።.
ይህም ቻይናን በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ የኢኮኖሚ ድቀት ብዙም ያልተሰማት ብቸኛዋ የዓለም አገር አድርጓታል።
ብዙ ኢኮኖሚስቶች በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የቻይና ኢኮኖሚ በፍጥነት ማንሰራራቱ አስገርሟቸዋል።
በ2020 በዓለም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በጠቅላላው በ42% ወድቋል።
ብዙውን ጊዜ የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚባለው አንድ የውጭ ኩባንያ በሌላ አገር ውስጥ ያሉ ኩባንያዎችን በመግዛት ወይም ከራሱ ኩባንያ ጋር እንዲጣመሩ በማድረግ ወይም በአዲስ ኩባንያ አዲስ ሥራ ለመጀመር መዋእለ ነዋዩን ማፍሰስ ሲጀምር ነው።