ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከዓመት በፊት ኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘባት ዉሃን ምን ላይ ትገኛለች?
በዉሃን ኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኘ ዓመት አለፈ።
መላው ዓለምን እንዳልነበረ ካደረገው ቫይረስ ጋር የፕ/ር ሺ ዢንግሊ ስም ተያይዞ ይነሳል።
ሳርስ-ኮቭ-2 ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ቫይረስ ነው ሲባልና ሌሎችም ጥያቄዎች ሲነሱ እኚህ ባለሙያም አብረው ይታወሳሉ።
ዉሃን ውስጥ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት እንደተገኘ መላምታቸውን በሳይንስ መጽሔት ይፋ አድርገዋል።
ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት ቫይረሱ በዉሃን ከመታየቱ በፊት ሌላ ቦታ ተከስቶ ነበር።
ቫይረሱ ወደ ቻይና፣ ዉሃን የገቡ ምግቦች ላይ መገኘቱን በመጥቀስ ነው ምናልባትም ቫይረሱ ከዉሃን ውጪ እንደገባ ያስረዱት።
መላምታቸው ብዙ ባለሙያዎችን ያነጋገረ ነው።
ቻይና ውስጥ ቫይረሱ የመጣው "ከአሜሪካ ነው" ብለው የሚያምኑ ዜጎችም አሉ።
አምና ጥር 23 የቻይና መንግሥት የዉሃን ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ፣ ትራንስፓርትም እንዲቋረጥ አዘዘ።
የጤና ባለሙያዎች መጀመሪያ ላይ ስለ ቫይረሱ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ሰሚ አላገኙም ነበር። ቻይናውያን መንግሥት ስለወረርሽኙ መረጃ ደብቋል ሲሉ ተችተውም ነበር።
ይህ ከሆነ ከዓመት በኋላ ዉሃን ተረጋግታ ወደ መደበኛ ሕይወት እየተመለሰች ነው።
ገበያ እየተሟሟቀ፣ ቫይረሱን ዉሃን ድል መንሳቷን የሚያወሳ ዐውደ ርዕይ እየተካሄደም ይገኛል።
ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ቫይረሱን በመታገል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ የሚጠቁም መልዕክት ተላልፏል።
በእርግጥ ቻይና በርካታ ዜጎቿን በመመርመር፣ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያደረጉ ሰዎችን በመለየትና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግ ስኬታማ ሆናለች።
በሌላ በኩል ደግሞ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦች ሰብአዊ መብት ጥሰዋል።
ቻይና ቫይረሱን በተመለከተ ማንኛውም ምርመራ እንዲደረግ ብትፈቅድም፤ አሁንም ቫይረሱ ከየት መጣ? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ መልስ አልተገኘም።
ከኮሮናቫይረስ በፊት የተቀሰቀሱ ወረርሽኞችን ያጠኑ ባለሙያዎች ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ ወደ ሰው ልጆች ተሸጋግሮ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
ቻይና ውስጥ ይህንን መላምት የተመረኮዘ ጥናት እምብዛም አልተሠራም።
"አደገኛው ቫይረስ ከየት እንደተነሳ ሳይታወቅ ወደቀደመው ሕይወት መመለስ አስጊ ነው" የሚሉት በኤምአይቲ እና ሀርቫርድ የቫይረስ አጥኚ የሆኑት አሊና ቻን ናቸው።
ቻይና ቫይረሱ ወደ ዉሃን የገባው ከሌላ ቦታ ነው የሚለውን መከራከርያ አጉልታ ማሰማቷን ቀጥላለች።
ሳይንሳዊ መረጃ ሳይኖር ቫይረሱ ወደ ዉሃን የመጣው ከሌላ ቦታ ነው ማለት ተገቢ ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የቻይና የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሁዋ ቹያንግ፤ "ጥያቄው ለቻይና ያለውን የተዛባ አመለካከት ያሳያል" ሲሉ መልሰዋል።
ቃል አቀባዩዋ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ይህ ቫይረስ አምና በአውስትራሊያ፣ በጣልያን እና በሌሎችም አገራትም መገኘቱን ነው።
ተመራማሪዋ አሊና በበኩላቸው ቫይረሱ ዉሃን ውስጥ ከመገኘቱ በፊት ሌላ ቦታ ስለመታየቱ ማስረጃ የለም ሲሉ ይከራከራሉ።
"የመጀመሪያዎቹ ታማሚዎች ከዉሃን ነበሩ። ከዚያም ከዉሃን ወጥተው የተጓዙ ሰዎች ላይ በሽታው ተገኘ" ይላሉ።
ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ብዙ ሳይንቲስቶችን ያከራከረ ጉዳይ ነው።
በአሜሪካ የበሽታ መከላከል ላይ የሚሠሩት ክርስቲን አንደርሰን፤ ቫይረሱ የታሸጉ ምግቦች ላይ ነው የተገኘው በሚለው ሐሳብ አይስማሙም።
የቻይናዋ ፕ/ር ሺ ዢንግሊ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ አምልጧል ብለው የሚያምኑ ባለሙያዎች ወደ ዉሃን ሄደው እንዲመረምሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ቻይና ከብዙ ወራት ቆይታ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት የምርመራ ቡድን ወደ ዉሃን እንዲሄድ ፈቅዳለች።
በዚህም አለ በዚያ ዉሃን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው ቫይረስ የመላው ዓለም ራስ ምታት ሆኖ ዓመት ደፍኗል።
የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች የዓለም ጤና ድርጅት ምርመራ አንዳች መልስ ይዞ እንደሚመጣ እየጠበቁ ነው።