የዩኬ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ከቀደመው የከፋ ነው ተባለ

በዩናይትድ ኪንግደም የተገኘው አዲስ የቫይረስ ዝርያ ከቀደመው የከፋ እንደሆነ ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የምርምር ውጤትን አጣቅሰው እንደተናገሩት፤ አዲሱ ዝርያ የከፋ እንደሆነ ምልክቶች ታይተዋል።

ምርምሩ የተካሄደው በቀደመው ኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር አዲሱ ዝርያ ከገደላቸው ጋር በማወዳደር ነው።

በፍጥነት የሚተላለፈው ዝርያ በዩኬ እየተሰራጨ ይገኛል።

"ቫይረሱ በፍጥነት ከመተላለፉም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ገዳይም ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት መግለጫ።

ፐብሊክ ኸልዝ አንግላንድ፣ ኢምፔርያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን እና ሌሎችም ግዙፍ የሕክምና ተቋሞች አዲሱ ዝርያ ምን ያህል ገዳይ እንደሆነ ጥናት እየሠሩ ነው።

የጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት፤ አዲሱ ዝርያ ቀድሞ ከነበረው የኮሮናቫይረስ አይነት በበለጠ አደገኛ መሆኑን ያሳያል።

የዩኬ መንግሥት የጤና አማካሪ ሰር ፓትሪክ ቫላንስ መረጃው "ገና አልተጠናከረም" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለ አዲሱ ዝርያ ግልጽ መረጃ ለማግኘት ተጨማሪ ምርምሮች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል የተሠራ ጥናት ቫይረሱ ከ30% እስከ 70% ተላላፊ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፤ አዲሱ ዝርያ ከዚህ 30 በመቶ በላቀ ሁኔታ እንደሚተላለፍ ተጠቅሷል።

ይህ ማለት 1,000 በ60ዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች በቀድሞው ኮሮናቫይረስ ቢያዙ የሚሞቱት 10ሩ ናቸው። ነገር ግን በአዲሱ ዝርያ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 13 ከፍ ይላል።

መስከረም ላይ የተገኘው አዲሱ ዝርያ አሁን በሰዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ወረርሽኝ ሆኗል።

የፋይዘር እንዲሁም የኦክስፎርድና አስትራዜኒካ ክትባቶች በዩኬ የተከሰተውን አዲስ ዝርያ ይከላከላሉ ተብሎ ይታመናል።

ነገር ግን በብራዚል እና በደቡብ አፍሪካ የተገኙት አዲስ ዝርያዎች አሳሳቢ እንደሆኑ የጤና ባለሙያዎች ጠቁመዋል።