ኮሮናቫይረስ ፡ የአውሮፓ ሕብረት የክትባት አቅርቦት ውዝግብ ቀጥሏል

ሁለተኛው የኮሮናቫይረስ ክትባት አምራች አቅርቦትን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የአውሮፓ ሕብረት የክትባት ስርጭትን ተስፋ አስቆራጭ አድርጎታል ተባለ፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም መድኃኒት አምራች የሆነው አስትራዜኔካ የምርት ችግር መኖሩን መጥቀሱ አቅርቦቱ ከሚጠበቀው በታች ይሆናል ማለት ነው፡፡

የአውሮፓ ኮሚሽን በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት እየሞከርኩ ነው ብሏል፡፡

በአንዳንድ የአውሮፓ ክፍሎች የፋይዘር-ባዮኤንቴክ ክትባት አቅርቦት በመቀነሱ ምክንያት ክትባቱ በመቆም ላይ ነው፡፡

ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጋር ክትባቱን የሚሠራው አስትራዜኔካ በመግለጫው ስለ ሁኔታውን ቢጠቅስም ዝርዝር ጉዳዮችን አልሰጠም፡፡

"በአውሮፓው የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ባለው የማምረቻ ጣቢያ ምክንያት ምርቱ መጀመሪያ ከሚጠበቀው በታች ይሆናል" ብሏል፡፡

ሮይተርስ ስማቸው ያልተጠቀሰ የአውሮፓ ሕብረት ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ እንደገለጸው፤ ኩባንያው በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ወደ ሕብረቱ ሊያደርስ ካሰበው የክትባት ብዛት ወደ 60 በመቶ የሚሆነውን ቅናሽ እንደሚያደርግ ለአውሮፓ ሕብረት ተናግሯል።

የአስትራዜኔካ ክትባት በአውሮፓ ሕብረት የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ዘንድ ገና ፈቃድ ባያገኝም በዚህ ወር መጨረሻ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

አስትራዜኔካ ቢያንስ 300 ሚሊዮን ክትባት ለማቅረብ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ተፈራርሟል፡፡

በመጋቢት ወር መጨረሻ ቃል ከተገባላቸው ሁለት ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባቶች፤ 600,000 ብቻ ማግኘቷን የኦስትሪያ ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ከወራት በኋላ ይደርሰሉ ተብሏል።

መዘግየቱ "ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም" ሲሉ የኦስትሪያው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሩዶልፍ አንሾበር ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካው ኩባንያ ፋይዘር፤ በቤልጅየም ያለው ፋብሪካውን አቅም ለማሳደግ እየሠራ በመሆኑ ለሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት የሚልከውን የክትባት መጠን እንደሚቀንስ አስታውቋል። የአውሮፓ ሕብረት 600 ሚሊዮን ጠብታ ከፋይዘር ለመግዛት ተስማምቷል፡፡

የፋይዘር ክትባት መቀነስ በጀርመን እና በጣሊያን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክልሎች የመጀመሪያዎቹን ክትባቶች እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል፡፡ በማድሪድ ለህክምና ባለሙያዎች የሚሰጠው ክትባትም ቆሟል፡፡

የክትባት ቅነሳን አስመልክቶ ጣልያን እና ፖላንድ ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን ብለው አስፈራርተዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት የኦክስፎርድ-አስትራዛኔካ ክትባትን ሳያጸድቅ መቆየቱ ያማረረው የሃንጋሪ መንግሥት፤ የአውሮፓ ሕብረትን ይሁንታ ባያገኝም በርካታ የስፑትኒክ ቪ ክትባ ለመግዛት ከሩሲያ ጋር ተስማምቷል።