ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ ሲወጡ ምን ለመሥራት አስበዋል?
ጃኑዋሪ 20 (ጥር 12)፣ ምሳ ሰዓት ላይ ትራምፕ ወደዱትም ጠሉትም ከነጩ ቤተ መንግሥት ይወጣሉ ተብሎ የሚጠበቅበት ዕለት ነው። ከዚያ በኋላ ግን ምን ሊሰሩ ነው?
ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር ከዋይት ሃውስ ኑሮ በኋላ ወደ ሰብአዊ ሥራ ውስጥ ገብተዋል። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ጎበዝ ሠዓሊ ናቸው። ብሩሽ ከያዙ አይለቁም።
ዶናልድ ትራምፕ ብሩሽም ሰብአዊ ሥራም ውስጥ የሉበትም። እንዲህ ዓይነት ነገር አያውቁም። ታዲያ በተቀረው ዕድሜያቸው ምን ሠርተው ይበላሉ?
አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምናልባት የሚከተሉትን ሊያደርጉ ይችላሉ።
1ኛ፦በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር
ትራምፕ አልተሸነፍኩም እያሉ ነው። አካሄዳቸው የሚገመት አይነት ሰው አይደሉም። ፍርድ ቤት ፋይል አስከፍተዋል። በባይደን መሸነፍ ሞት ሆኖባቸዋል። ጠበቆቻቸው ፋታ የላቸውም። ይህ በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ ያልታየ ባሕሪ ነው።
ምናልባት ይፈርድልኛል ያሉት ፍርድ ቤት ፈርዶባቸው የሽንፈትን ጽዋ ጠጥተው ለጊዜው ከዋይት ሐውስ ቢወጡ፥ 4 ዓመት ጠብቀው በቀለኛ ሆነው ሊመለሱ ይችላሉ።
በአሜሪካ ታሪክ ግሮቨር ክሌቭላንድ ብቻ ናቸው ከዋይት ሐውስ ወጥተው ወደ ዋይት ሐውስ ተመልሰው የገቡት መሪ።
22ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ። 23ኛው ሌላ ፕሬዝዳንት መጣና በ24ኛው ተመልሰው መጡ።
ፕሬዝዳንት ክሌቭላንድ ይህን ያደረጉት ከበርካታ ዓመታት በፊት ነው። በ1885 እንደነሱ አቆጣጠር አካባቢ ለ4 ዓመታት አሜሪካንን መሩና ተሸንፈው ወጡ። ከዚያ መልሰው በ1893 ተመልሰው መጡ።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ማንኛውም ፕሬዝዳንት ከ2 ጊዜ በላይ በፕሬዝዳንትነት ሊያገለግል አይችልም ይላል። ነገር ግን ሁለት ጊዜ ብቻ የሚለው የግድ በተከታታይ መሆን አለበት አይልም።
ስለዚህ ትራምፕ ጨክነው ለባይደን ነጩን ቤተ መንግሥት ለ4 ዓመት ከለቀቁ በኋላ ተመልሰው ደግሞ ባይደንን ሊያስለቅቋቸው እንደሚችሉ ረዳቶቻቸው ከወዲሁ መተንበይ ጀምረዋል።
የቀድሞው የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚክ ሙልቫንሊ እንደሚሉት በ2024 የፕሬዝዳንት እጩዎች መሀል የትራምፕ ስም መኖሩ የሚጠበቅ ነው።
ትራምፕ በጣም ከሚያስደስታቸው ነገር አንዱ ቅስቀሳ ማድረግ ነው። ደጋፊዎቻቸው ስማቸውን እየዘመሩ ሲያሞካሸዋቸው ደስታ ይወራቸዋል።
በዚህ ተሸነፉበት በተባለው ምርጫ ያገኙት ድምጽ ቀላል አይደለም። 71 ሚሊዮን አሜሪካዊያን ፈቅደዋቸዋል።
ይህ ቁጥር ለተሸናፊ ፕሬዝዳንት ክብረ ወሰን ነው። ይህ አሐዝ የሚነግረን ትራምፕ ከባድ የሆነ የደጋፊ መሰረት እንዳላቸው ነው። ታዲያ በ2024 ለምን ተመልሰው አይመጡ?
በነገራችሁ ላይ የፕሬዝዳንቱ የበኩር ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይሻል። መቼ የሚለው ነው የማይታወቀው።
2ኛ፦ ጎበዝ ነጋዴ መሆን
ትራምፕ ፖለቲከኛ ከመሆናቸው በፊት እውቅ የቢዝነስ ሰው ነበሩ።
በሪልስቴት የሚያህላቸው የለም። በእውናዊ የቲቨ ትእይነት ደግሞ ዝናንም ገንዘብንም አትርፈዋል። ያፈሱት ዶላር ስፍር ቁጥር የለውም።
አሁን ደግሞ ከዋይት ሐውስ ወጥተው ወደ ንግዱ ሲመለሱ የዝና ማማቸው ከትራምፕ ታወር ከፍ ብሎ ነው የሚጠብቃቸው። ለምን ቢባል ማንኛውም ቢዝነስ አጋራቸው እየሰራ ያለው አሜሪካንን ለ4 ዓመታት ከመራው ትራምፕ ጋር ነዋ።
ትራምፕ ባለጸጋ ይሁኑ እንጂ በእዳም ተተብትበዋል። እርግጥ ነው እዳ የሌለበት ሀብታም ላይኖር ይችላል። ቢሆንም ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው ትራምፕ ተራራ የሚያህል የእዳ ቁልል አለባቸው። በሚቀጥለው ዓመት ብቻ መመለስ የሚጠበቅባቸው ግማሽ ቢሊዮን ዶላር እዳ ተከማችቶባቸዋል።
ትራምፕ ግን ይህ የምትሉት ገንዘብ እኮ ከኔ ሀብት ጋር ብታነጻጽሩት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲሉ ተሳልቀዋል፣ በጋዜጣውና አጋሮቹ።
የትራምፕ ድርጅት በዋናነት ሆቴሎችና የጎልፍ መጫወቻ መዝናኛዎችን የያዘ ነው። ይህ ንብረት በአሜሪካም በአውሮፓም የሚገኝ ነው።
በትራምፕ የንግድ ስም የሚገኙ ሆቴሎችና የጎልፍ መዝናኛዎች በሕንድ ሙምባይ፣ በቱርክ ኢስታንቡል እና በፊሊፒንስ በዱባይና ኢንዶኔዥያ አሉ። በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችም እንዲሁ።
ትራምፕ ወደ ንግዳቸው ልመለስ ካሉ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ምክንያቱም ብዙዎቹ የርሳቸው ንብረቶች ከመዝናኛና ሆቴል ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህን ኢንዱስትሪ ደግሞ ኮሮና አዳክሞታል።
ፎርብስ እንደሚለው ትራምፕን ኮቪድ ይዞ ለቋቸዋል። ቢዝነሳቸውን ግን አለቀቀውም። ኮቪድ 1 ቢሊየን ዶላር አካባቢ ሳያሳጣቸው አልቀረም።
ኒው ዮርክ ታይምስ በበኩሉ ትራምፕ ከባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ በ10 ዓመታት ግብር አልከፈሉም ሲል ጽፏል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግብር ስወራም ይታማሉ። የሚሰውሩት ግን የሕግ ቀዳዳን ተከትለው ነው። ትራምፕ ግብር ለመሰወር የተገደዱበት ዋናው ምክንያታቸው ድርጅታቸው ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ ውስጥ ስለተንሳፈፈ ነው ይላል ጋዜጣው።
3ኛ፦ የሚዲያ ባለቤት መሆን
ትራምፕ ለቴሌቪዥን አዲስ አይደሉም። አፓረንቲስ የእውናዊ ኩነቶች የቲቪ ትእይንት ነበር። ከአሜሪካ አልፎ ለዓለም እውቅና አብቅቷቸዋል፥ ተራምፕን።" ዩ አር ፋየርድ" እያሉ ተወዳዳሪዎችን ሲያባርሩ በሚሊዮኖች ተመልካቾች አእምሮ ቀርተዋል።
ይህን ተከትሎ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ በኋላ አዲስ የቲቪ ቻናል ይጀምራሉ የሚሉ ግምቶች ተንሰራፍተዋል።
የራሳቸውን የቲቪ ጣቢያ ባይከፍቱ እንኳ ካሉት ጋር በቅንጅት የራሳቸውን ትዕይንት ሊጀምሩ ይችላሉ።
ትራምፕ ምን ዓይነት የቲቪ ትእይነት ሊጀምሩ ይችላሉ የሚለው እያነጋገረ ነው።
ምናልባት እንደ ካርዳሺያን ያለ ወይም የሀዋርድ ስተርን ዓይነት ትእይነት ሊያስቡ ይችላሉ። በግለሰብና በቤተሰብ ዕለታዊ ሕይወት ላይ ያተኮረ።
ኬብል ኒውስ፣ ኒወስማክስ አሜሪካ ኒውስ ኔትወርክ ለትራምፕ የአብረን እንሥራ ጥያቄ ሊያቀርቡ ይችላሉ።
የኒውስማክስ ኃላፊ ክሪስቶፈር ሩዲ የትራምፕ ሚስጢረኛ ይባላሉ። ምናልባት ወደሱ ሊያደሉም ይችላሉ።
ትራምፕ ከዋይት ሐውስ በኋላ መጽሐፍ እንዲጽፉ የስምምነት ገንዘብ ሊቀርብላቸውም ይችላል።
ይህ ለተሰናባች ፕሬዝዳንቶች የተለመደ ነው።
ባራክና ሚሼል 65 ሚሊዮን ዶላር ነበር የቀረበላቸው። በዚህ ረገድ ክብረ ወሰኑም የነሱ ነው። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ 10 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሏቸዋል።
ክሊንተንም ቢሆን የፖድካስት ስርጭት ስምምነትን ፈርመው ያውቃሉ።
ኦባማ ከኔትፍሊክስ ጋር የሚሊዮን ዶላሮች ስምምነት አድርገዋል። ትራምፕም ይህንኑ ማድረጋቸው የማይቀር ነው።
መጽሐፉን እሳቸው ባይጽፉት እንኳ "ሥውር ደራሲ" ቀጥረው ሊያጽፉት ይችላሉ። ብዙዎች ተሻምተው የሚያነቡት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
4ኛ፦ አርፈው ጡረታቸውን ማስከበር
ትራምፕ ለተሰናባች ፕሬዝዳንቶች የሚሰጠው የጡረታ አበል ብቻውን አንቀባሮ ያኖራቸዋል። እንደው በቃኝ ምን አንቀዠቀዠኝ ብለው አርፈው መቀመጥ ቢያምራቸው ማለት ነው።
የ1958 ደንብ ለተሰባች ፕሬዝዳንት ክብሩን የሚመጥን ገንዘብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንዲቀርብ ያዛል።
በዓመት 200ሺ ዶላር እና ከዚያ በላይ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር የሚሰጥ የፕሬዝዳንታዊ ጡረታ ብር አለ።
በዚያ ላይ የሲክሬት ሰርቪስ የዕድሜ ልክ የልዩ ጥበቃ አገልግሎት ይቀርብላቸዋል። የጤናና የጉዞ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችም ይቀርቡላቸዋል።
ስለዚህ ትራምፕ ሁሉን ነገር በቃኝ ብለው በ74 ዓመታቸው የተረጋጋ የጡረት ሕይወት ሊመሩ ይችላሉ።
አልፎ አልፎ ደግሞ ዩኒቨርስቲዎች እየሄዱ በትርፍ ሰዓታቸው ንግግር ቢያደርጉ በርካታ ገንዘብ መሥራትም ይችላሉ።
የተረፈውን ጊዜ ደግሞ የሚወዱትን ጎልፍ በፍሎሪዳ ማሬላጎ የባሕር ዳርቻ ሊጫወቱ ይችላሉ።
ነገር ግን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ረዳቶች ይሄ ለትራምፕ በፍጹም የሚስማማ የሕይወት ዘይቤ አይደለም ይላሉ።
ምክንያቱን ተናገሩ ሲባሉ "ትራምፕ ጭር ሲል የሚወዱ ሰው አይደሉም።" ይላሉ።