ባህሬይንን ለ49 አመታት በመምራት በአለም ቀዳሚ የሆኑት መሪ አረፉ

ባህሬይንን ለ49 አመታት በመምራት በአለም የቀዳሚነቱን ቦታ የያዙት ልዑል ካሊፋ ቢን ሰልማን አል ከሊፋ በ84 አመታቸው ከዚህች አለም በሞት ተለይተዋል።

ልዑል ከሊፋ ባህሬይን ነፃነቷን በተቀዳጀችበት ከጎሮጎሳውያኑ 1971 ጀምሮም አገራቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ ነበር ተብሏል።

ባደረባቸውም ህመም ህክምና በአሜሪካ ሲከታተሉ እንደነበርም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የንጉስ ሃማድ አጎት የሆኑት ልዑል ከሊፋ በአገሪቱ ባለው የንጉሳውያን ቤተሰብ ስርአትም ከፍተኛ ቦታ እንዳላቸውም ተገልጿል።

ልዑሉን ከስልጣን ለማውረድ በሚል የዲሞክራሲ ደጋፊዎች የአረብ ስፕሪንግን አመፅ በማንሳት በጎሮጎሳውያኑ 2011 ከፍተኛ ተቃውሚ ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል።

ልዑሉ በበኩላቸው የአረብ ስፕሪንግ ማምጣት የቻለው "ሞት፣ ቀውስና ጥፋት" ነው በማለት የፖለቲካ ማሻሻያዎችን አልቀበልም በማለት በእምቢተኝነታቸው ፀንተዋል የሚለውንም አይቀበሉትም።

ልዑሉን በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ እሳቸውን የሚተካቸው መሪም ይህንኑ ያስቀጥላል ወይ የሚለውን ጥያቄ ተንታኞች እያነሱም ይገኛሉ።

በሱኒ ሙስሊሞች ቁጥጥር ስር ያለው አመራር በስርአቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ተቃዋሚዎችን ዝም በማሰኘት የሚተች ሲሆን በተለይም ከዘጠኝ አመት በፊት ካልተሳካው የአረብ ስፕሪንግ ጋር ተያይዞም በከፍተኛ ሁኔታ ቀጥሏል።

ተቃውሞውን በዋነኝነት ሲመሩ የነበሩት የሺያ ሙስሊሞች ናቸው።

መንግሥት የግል ሚዲያዎችን ከመዝጋት በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አፈራርሷል እንዲሁም ትችቶችንም አይታገስም ይባላል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና እንዲሁም መንግሥትን የሚተቹ ግለሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም የባህሬይን ዜግነታቸውን የተነጠቁ ሲሆን አምስት ግለሰቦችም በሽብር ወንጀል በሞት ተቀጥተዋል። በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ይህንኑ አውግዘውታል።