ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ሥልጣን አለቅም ቢሉ በአሜሪካ ምን ይከሰታል?
በአሜሪካ 244 ዓመት የፖለቲካ ታሪክ ሥልጣን አለቅም ብሎ ያለ አንድም ፕሬዝዳንት አልተወለደም። ትራምፕ ግን እያስፈራሩ ናቸው። ነገሩን ሁሉ ወደ ፍርድ ቤት እየወሰዱት ነው።
ቆጠራው ይደገም፣ ተጭበርብሯል፣ ታዛቢዎች ሲጭበረበር እንዳያዩ ተደርገዋል፣ እከሳለሁ፣ ባይደን አላሸነፈኝም፤ የአሜሪካ ሚዲያ ነው ያሸነፈኝ እያሉ ናቸው።
በየዕለቱ ገና ምን አይታችሁ እያሉ ይዝታሉ። ታዲያ ምን ተሻለ?ባይደን አሸነፉ ተብሎ አገር ጉድ ሲል ትራምፕ ቨርጂኒያ ነበሩ። ጎልፍ ይጫወቱ ነበር።
ወዲያውኑ የፕሬዝዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን “ባይደን አሸነፈ ያለው ማነው? ገና እንተያያለን”የሚል መግለጫ አወጣ። አሜሪካዊያን ግራ ተጋቡ። እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሟቸው አያውቅማ።
ታዲያ አሁን ምን ተሻለ?
ከዋይት ሐውስ ነቅነቅ አልልም ቢሉስ፣ ትራምፕ? እዚሁ ቅበሩኝ ቢሉስ ትራምፕ?የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አንድ ቁልጭ አድርጎ የሚያስቀምጠው ነገር አለ፤ በጥር (ጃንዋሪ) ወር በዕለት 20፣ ዕኩለ ቀን ላይ የተሸናፊው ፕሬዝዳንት ሥልጣን ይለቃል፣ ከነጩ ቤተ መንግሥትም ማቄን ጨርቄን ሳይል ይወጣል።
ጆሴፍ ባይደን ከዋና ዋና ግዛቶች ለፕሬዝዳንትነት የሚያበቃቸውን የውክልና ድምጽ አግኝተዋል። ከ270 የአሸናፊነት መስመርም አልፈዋል። እንዲያውም በአሜሪካ ታሪክ እንዲህ በርካታ የሕዝብ ድምጽ ያገኘ ተወዳዳሪ የለም።
ባራክ ኦባማ ራሱ ተበልጠዋል። ችግሩ ወዲህ ነው። ትራምፕ የሽንፈትን ጽዋ ግጥም አድርጎ መጠጣት አይችሉም። በቃ አይችሉም።
ስለዚህ በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙትን ሰው ድል ለመቀበል አልቻሉም። ስለዚህ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ተሸጋገሩ። ምርጫው ተጭበርብሯል ወደሚለው ምዕራፍ። ይህን ደግሞ መፋለም የሚችሉት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሳቸው ወዳጆች፣ በወግ አጥባቂ ዳኞች የተሞላ ነው። ነገሩን እዚያ ካደረሱት ያልተጠበቀ ነገር ሊከሰት ይችላል።ትራምፕ አሁን ከፍተኛ ሚሊዮን ዶላር መድበው፣ እሳት የላሱ ጠበቆቻቸውን አሰልፈው 'ዳይ' ፍርድ ቤት ክስ መዝገብ ክፈት እያሉ ነው።
ሩዲ ጁሉያኒ የጠበቆቻቸው አለቃ ናቸው።
ትራምፕ አሁን ላይ የሕግ ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ፣ ምርጫው ላይ ከሕግ ያፈነገጡ ነገሮች ከነበሩና ይህን በማስረጃ ማስደገፍ ከቻሉ ነገሮች እንዳልነበሩ ሊሆን ይችላሉ።
ገና ከአሁኑ ዳግማዊ ቆጠራ የታዘዘላቸው ግዛቶች አሉ።የሚገርመው ትራምፕ ምርጫው ተጭበረበረ ማለት የጀመሩት ግን ምርጫው ገና ከመጀመሩ፣ ድምጽም ከመሰጠቱ በፊት ነው።
“እኔ ልሸነፍ የምችለው ምርጫው ከተጭበረበረ ብቻ ነው” ያሉት ገና የባይደን ድል ከመሰማቱ ቀደም ብሎ ነበር።አሁን የአሜሪካ ሚዲያ “ሰውየው ከዋይት ሐውስ የምርም አልወጣ ቢሉስ?” በሚል እየቃዠ ነው።
ይህ ነገር በሌላ ጊዜ ቢሆን በአሜሪካ ለፌዝ እንጂ ለቁምነገር የሚነሳ ጉዳይ አልነበረም።የፖለቲካ ኮማኪዎች እንጂ የፖለቲካ ጋዜጠኞች እንዲህ ቧልት የሚመስል ነገር አያነሱም ነበር። የትራምፕ ዘመን ግን ግራ የሚያጋባ ነው።
ስለዚህ ይሄ ነገር ገና ቀደም ብሎ ነው አሳሳቢ የሆነው።ለምሳሌ በሰኔ ወር ላይ ጨዋታ አዋቂው ትሬቨር ኖዋ ለባይደን “በምርጫ ቢያሸንፉና ሆኖም ግን ባላንጣዎ ትራምፕ ከቤተ መንግሥት አልወጣ ቢልዎትስ?” በሚል በወቅቱ አስቂኝ የነበረ ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር።
“ለመሆኑ እጩ ፕሬዝዳንት ባይደን በዚህ ጉዳይ ላይ አስበውበታል??” አላቸው። ትሬቨር ኖዋ ለባይደን። “እውነት ለመናገር አስቤበታለሁ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ መከላከያው ጣልቃ ገብቶ ነገሮችን ሊያስተካክል ይችል ይሆናል”ብለውት ነበር።
ባይደን ያኔ ሰኔ ላይ ይህንን ሲሉ ዛሬ የሆነው ነገር ይሆናል ብለው አስበዋል ለማለት ይከብዳል። ባይደን ደግመው ደጋግመው እንደሚሉት ድምጽ ሰጪው ሕዝብ ነው እንጂ እጩዎች አይደሉም የምርጫ ውጤት ምን መሆን እንዳለበት የሚወስኑት።
ምናልባት ትራምፕ ከቤተ መንግሥት አልወጣም ካሉ የአሜሪካ ሲክሬት ሰርቪስ (የደህንነት አገልግሎት) ነገሩን ይቆጣጠራል። ሲክሬት ሰርቪስ (የደህንነት አገልግሎት) የሚባለው ከወታደራዊ ተቋም ያልሆነ፣ ሁነኛ ሥራው የፕሬዝዳንቱን ደህንነት የሚጠብቅ አካል ነው።
ይህ ልዩ የደህንነት አካል ታዲያ ፕሬዝዳንቱ ፕሬዝዳንት ሳሉ ብቻም ሳይሆን ከዋይት ሐውስ ከለቀቁ በኃላም ለፕሬዝዳንቱ ጥበቃ እንዲያደርግ በሕግ ይገደዳል።
ለዚህም ነው አሁን ተመራጭ ፕሬዝዳንት ለሆኑት ባይደን ምንም እንኳ ዋይት ሐውስ መግቢያቸው ገና ቢሆንም የሲክሬት ሰርቪስ ጥበቃ አገልግሎትን እየሰጣቸው የሚገኘው።
ቢቢሲ ነገሮች እንዳው የከፉ ቢሆኑ ምን ሊከሰት ይችላል በሚል በጉዳዩ ዙርያ አዋቂዎችን አነጋግሮ ነበር። ፕሮፌሰር ዳኮታ ሩደሲል በአገር ደህንነት ፖሊሲ ኦሐዮ ስቴት ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው።
“ትራምፕ እምቢ ቢሉ አሜሪካ ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል። የዲሞክራሲ ተምሳሌት በምትባል አገር ይህ ከሆነ መቼስ የሚደንቅ ነው? ይላሉ ፕሮፌሰሩ። ይህ የመሆኑ ዕድል ግን እጅግ ጠባብ ነው ባይ ናቸው።
“ወታደሩ ትራምፕን ሊደግፋቸው አይችልም። ወታደሩ ታማኝነቱ ለሕገ መንግሥቱ ነው። ለፕሬዝዳንቱ አይደለም። ስለዚህ ትራምፕ ብቻቸውን ይቀራሉ” ብለውም ያስባሉ፣ ፕሮፌሰሩ።
ከርሳቸው ጋ የሚስማሙት የፒትስበርግ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ኬይሸ በሌይን ናቸው።“ትራምፕ አያረጉትም ባይባልም ይህ ነገር የመሆን እድሉ የጠበበ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ኬይሸ።
“ትራምፕ በቅርብ ጊዜ በተነሱ ተቃውሞዎች ወታደር ማሰማራታቸው አይዘነጋም። አሁንም ከቤተ መንግሥት አልወጣም ብለው ወታደሩን ሊያሰማሩ ቢችሉስ የሚለው በጣም የራቀ ሀሳብ ነው” ፕሮፌሰር ሩድሲል የሚያሳስባቸው ፕሬዝዳንቱ ከቤተ መንግሥት አልወጣም ይላሉ ብለው ሳይሆን የሕዝብ ለሕዘብ ግጭቶች እንዲከሰቱ ፕሬዝዳንቱ ምክንያት እንዳይሆኑ ነው።
“በአንድ ጽሑፌ ላይ ገልጨዋለሁ። ትራምፕ ፍጹማዊ ሥልጣናቸው ሳያበቃ በፊት የመንግሥት መዋቅሩን ወይም ደግሞ የፍትሕ ዲፓርትመንቱን የሚያዝ ልዩ መመርያ ሊያወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ምርጫው አሸናፊው እኔ ነኝ ስለዚህ የምትታዘዙት ለኔ ነው የሚል”ይህንን ካደረጉ ወታደሩ ከአስፈጻሚው ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባቱ አይቀርም።
አሁን ከፕሬዝዳንቱ ሽንፈትን አለመቀበል በላይ አሳሳቢ የሆነው ለደጋፊዎቻቸው፣ አይናቸውን ጨፍነው ትራምፕ ወይም ሞት ለሚሉት ደጋፊዎቻቸው ለአመጽ የሚገፋፋ ጥሪ እንዳያቀርቡ ነው። ዶናልድ ትራምፕ ይህን ካደረጉ የአሜሪካ ከተሞች ታይቶ በማይታወቅ ግጭት ሊታመሱ ይችላሉ።
ትራምፕ ደግሞ አያደርጉትም አይባልም።