ፓናማ፡ ባለሥልጣኑ እጽ በመኪናቸው ጭነው ሲሄዱ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/@PROTEGERYSERVIR
የፓናማ ፖሊስ 79 ፓኮ እሽግ አደገኛ እጽ መያዙን ይፋ አድርጓል፡፡
የአገሬው ሚዲያ ይህንን ያህል እሽግ እጽ በመኪናቸው ደብቀው ሲሄዱ ከተያዙት መካከል አንድ ባለሥልጣን እንዳሉበት ገልጸዋል፡፡
የጉና ያላ ግዛት ገዥ የሆነት ኤሪክ ማርቴሎ ናቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡
ፖሊስ ጥቆማ ደርሶት ድንገት አሰሳ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ አሰሳውን ያደረገው ዋና መንገድ በመዝጋትና መኪናዎችን በመበርበር ነበር፡፡
አደገኛ እጾቹ የተገኙት በመኪናው መቀመጫዎች ሥር ተወትፈውና ተጠቅጥቀው ነው፡፡
የፓናማ ፕሬዝዳንት ኒቶ ኮርቲዞ በትዊተር ገጻቸው በስፓኒሽ ቋንቋ ‹‹እኛ የሕዝብ አገልጋዮች ነን፤ ማንኛውንም ከመስመር የወጣ ባለሥልጣን አንታገስም›› ብለዋል፡፡
እስካሁን ለሚስተር ማርቴሎም ሆነ ከጠበቃቸው በጉዳዩ ላይ ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡
ጉና ያላ ግዛት የምትገኘው በፓናማ የካሪቢያን ጠረፍ ሲሆን ጉና የሚባሉ የአገሬው ነባር ዜጎች መኖርያ ናት፡፡
ጉና ያላ በደቡብ ከኮሎምቢያ ትዋሰናለች፡፡ በዚህም የተነሳ ከድሮ ጀምሮ ለአደገኛ እጽ አስተላላፊዎች እንደ ዋንኛ መመላለሻ ሆና ታገለግላለች፡፡












