ኮሮናቫይረስ ፡ በአፍሪካ ከሚደረገው የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር ጀርባ ያለችው ኢትዮጵያዊት

ምህረት አማረ

የፎቶው ባለመብት, MIHRET

ምህረት አማረ ሱዳን ውስጥ ተወልዳ እድገቷ አሜሪካ ሲሆን፤ አሁን በሥራዋ አማካኝነት አፍሪካ ውስጥ መሥራቷ እንደሚያስደስታት ትናገራለች።

ምህረት አማረ ለአሥር ዓመታት በቁስልና በቆዳ ሪጄነሬሽን [ማገገም] የህክምና ላይ በመሰማራት ትሠራ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በኮቪድ-19 ክትባት ምርምር ላይ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።

በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ተመርቃ በጥናትና ምርምር ላይ አትኩራ እየሠማራች ያለችው ለተለያዩ በሽታዎች መፍትሔ ለማግኘት ካላት ፍላጎት እንደነበር ትገልፃለች።

ምህረት ለ10 ዓመታት በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ከሠራች በኋላ ፍላጎቷን ሰፋ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰቱና አሳሳቢ ለሆኑ የጤና እክሎች መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ወደሚደረግበት ዘርፍ መዘዋወርን መረጠች።

ይህንንም ተከትሎ ወደ ትምህርት ዓለም በመመለስ ሁለተኛ ዲግሪዋን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በማጠናቀቅ ወደ ጥናትና ምርምር ፖሊሲ ማኔጅመንት ተዘዋወረች።

በምርምር ተቋሙ ውስጥም ምክትል ዳይሬክተር ሆና በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ዙሪያ በአህጉሪቱ ውስጥ በመሥራቷ ኩራት እንዲሰማት ከማድረጉ በላይ አፍሪካዊት በመሆኗ ደግሞ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጣት ትናገራለች።

"እንዲህ ዓይነት ሥራ ላይ ስንሰማራ ባህልን መመልከት ያስፈልጋል" የምትለው ምህረት የምታከናው ተግባራ የተሳካ እንዲሆን አፍሪካዊ መሆኗ በጣም እንደሚጠቅማት ታምናለች።

በዚህም አሁን እየሰራችበት ያለው የሄንሪ ጃክሰን ፋውንዴሽንም ሆነ "ለአህጉሪቱ ጥሩ ነገር እያበረከትኩ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ" ስትል ምህረት ትናገራለች።

ዋልተር ሪድ አርሚ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሪሰርች ወይም ውሬይር በመባል የሚታወቀው ድርጅት በአፍሪካ ውስጥ ከተሰማራ 50 ዓመት የሆነው ሲሆን ምህረት የምትሰራበት ድርጅት ደግሞ ይህንኑ የምርምር ተቋም የሚያግዝ ፋውንዴሽን ነው።

በእዚህ ውስጥ የምህረት የሥራ ድርሻ የሚደረጉ የጥናት ፕሮግራሞችን በበላይነት መቆጣጠር ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ጥናትና ምርምር የሚደረገውን ሩጫ በቅርብ የመከታተል ኃላፊነት አላት።

"ሥራችን በላይቤሪያ፣ በጋና እና በናይጄሪያ ላይ የሚያተኩር ነው" የምትለው ምህረት ከ6 ዓመታት በፊት ብዙ ሰዎች ለሞት የዳረገውን የኢቦላ በሽታ በቅርበት በመመልከት ወረርሽኙ አጥቅቷቸው የነበሩ አገራት ውስጥ ያሉትን የጤና ተቋማትን የማጠናከር አስፈላጊነት መረዳታቸውን ትገልፃለች።

ይህ በተለይ በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ አገራት ውስጥ ከተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ብዙ ልምድና ትምህርት መወሰድ መቻሉንም ምህረት ትናገራለች።

ምህረት ከባልደረቦቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, MIHRET

በዚህም ምክንያት "በአፍሪካ ውስጥ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ ጉዳት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ተሞክሮውን እንደ ልምድ በመውሰድ ለኮቪድ-19 እየጠቀመን ነው" ትላለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተስፋፋ ጀምሮ የምህረት ሥራ ለኮቪድ-19 ክትባት ጥናት የሚያስፈልገውን እርዳታ ከማበርከትም በተጨማሪ ለህክምና ባለሙያዎች የሚያስፈልጉ የመከላከያ አልባሳትን (ፒፒኢ) እና ጭምብሎችን የመሳሰሉ መገልገያዎችን ለተለያዩ ማዕከላት እንደሚያበረክቱና ሥልጠናዎችንም እንደሚሰጡ ትናገራለች።

በአሁን ጊዜ በውሬይር ሥር እየተመራ ያለውን የኮሮናቫይረስ የክትባት ምርምር ለምዕራብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው አህጉሩ እንዲዳረስ በማሰብ ጥናቱ እየተካሄደ መሆኑን ትገልፃለች።

"ጥናቱን መምራት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የሥራው ሂደት ውጤታማ በሆነ አቅጣጫ በመጓዝ ላይ በመሆኑ ደስተኞች ነን። በተለይ በእንስሳት ላይ ስናካሂድ የነበረው ምርምር የፈለግነውን ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከያ አቅም [ኢምዩኒቲ] የመጎልበት ምልክቶች እያሳየ ነው" የምትለው ምህረት ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላም ሙከራው ወደ ሰው እንደሚያድግ ጠቁማለች።

በምዕራብ አፍሪካ ያሉት ቤተ ሙከራዎች ቀደም ሲል ለምርምርና ለሙከራ አስፈላጊ የሆኑ መሣሪዎች ያልነበራቸው ሲሆን፤ ምህረት አማረ በምትመራው ፕሮግራም ሥር ጥናትና ምርምሩን ለማሳካት የሚያስፈልገውን በሙሉ ማሟላት መቻላቸውን ትናገራለች።

በዚህም ምክንያት "ከአካባቢ አገራት ይወሰዱ የነበሩ ናሙናዎች ወደ ሌላ በመላክ ይደረግ የነበረው ምርመራ ቀርቶ፤ አሁን የተሟላ ቤተ ሙከራ በመኖሩ ሁሉም ምርመራ እዚሁ መደረግ ተችሏል" የምትለው ምህረት የክትባት ጥናቱ የመጀመሪያው ዙር ምርምር በምዕራብ አፍሪካ ከተደረገ በኋላ "የሁለተኛው ዙር የመጨረሻ ፍተሻና ማረጋገጫው አሜሪካ በሚገኙ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ይከናወናል" ብላለች።

እንደ ምህረት ምልከታ በኮሮናቫይረስና በሌሎች በሽታዎች ላይ ጥናትና ምርምር በሚካሄድባቸው በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ የተለየውና የሚያስደምመው ነገር መላው ሠራተኞች አፍሪካውያን መሆናቸው ነው። "ናሙናውን ከሚሰበስቡት ጥናትና ምርምር እስከሚያደርጉት ባለሙያዎች በሙሉ አፍሪካውያን ነን" ትላለች።

ጨምራም ማዕከላቱ አሜሪካ ውስጥ ካሉት አቻ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ "ለጊዜው ወደ ክትባት የሚያመሩት ሥራዎች በአሜሪካ እየተሠሩ ቢሆንም ሥራው በትብብር የሚሠራ በመሆኑ ጥረቱ ፍሬያማ ቢሆን የሁሉንም ድርጅቶች ስም የሚያስጠራ የጋራ ውጤት ነው" በማለት ትገልጻለች።

ባለንበት ዘመን መላውን ዓለም ያስጨነቀውን የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት በአፍሪካ ውስጥ የሚደረገውን ጥረት ከሚያስተባብሩት ባለሙያዎች መካከል አንዷ የሆነችው ምህረት ወደ ሳይንሱ ትምህርት እንድታዘነብል የወላጆቿ ግፊት ወሳኝ ሚና እንደነበረው ታምናለች።

ምህረት አማረ

የፎቶው ባለመብት, MIHRET

ምህረት በመጀመሪያ የሕክምና ዶክተር የመሆን ፍላጎት ኖሯት ተነስታ ከዘርፉ ሳትርቅ በመካከል ላይ ግን በዶክተርነት ማዕረግ ወደ የላቦራቶሪው ዘርፍ ልቧ ማዘንበሉን ትናገራለች።

"በማይክሮስኮፕ ውስጥ የሚታየውን ዓለም የማየት ዕድሉን ካገኘሁበት ጊዜ አንስቶ ከሕክምና ወደ ላቦራቶሪ ሥራው ገብቼ ለዓመታት ቆይቻለሁ" በማለት ጅማሬዋን ታስታውሳለች።

በዘርፉ ሴቶችን የሚያበረታታ ነገር እንዳልነበረ የምትናገረው በጀመረችው ለመግፋት አላመነታችም ነበረ "ምንም ነገር፤ ማድረግ ከምፈልገው ነገር እንዲገታኝ አልፈቅድም" የምትለው ምህረት ህልሟን ለማሳካት ወደ ዘርፉ ማኔጅመንት እንድታዘነብል እንዳደረጋት ትናገራለች።

ይህንን ለውጥ ለማድረግ እየተዘጋጀች በነበረችበት ወቅት ውሳኔዋን ያወቁ ባልደረቦቿ በነበረችበት የላቦራቶሪ ሥራ ላይ እንድትቆይ ይመክሯት እንደነበር የምትናገረው ምህረት እሷ ግን ፍላጎቷን እውን ለማድረግ በውሳኔዋ መፅናቷን ታስረዳለች።

ምህረት ለዘርፉ የሚያስፈልጋትን ትምህርቷን [ኤም.ቢ.ኤ] አጠናቃ አሁን እየመራችው ባለው የጥናትና ምርምር ሥራ ውስጥ መገኘቷ በጣም ደስተኛ እንዳደረጋት በኩራት ትናገራለች።

"ወደ ትምህርት ተመልሼ ለመማር ስወስን ልጅ እያሳደኩኝ ነበረ። ሁኔታው በተወሰነ ደረጃ ፈታኝ ቢሆንም የማይቻል ሆኖ አላገኘሁትም" በማለት ሴቶች በተለያዩ ኃላፊነቶች ውስጥ ሆነው እንኳን ያሰቡትን ማሳካት እንደሚችሉ የእራሷን ተሞክሮ በመጥቀስ የደረሰችበትን ታወሳለች።

ወደፊት ደግሞ "ብችል ለአፍሪካ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት እመኛለሁ" የምትለው ምህረት፤ "ሲጀመር አሁን የምሠራበትን ድርጅት የተቀልቀልኩት ቀስ በቀስ ወደ አገር ቤት እንዲወስደኝ በማሰብ ነው" ትላለች።

ምህረት በትምህርቷና በሥራዋ ያሳካችውን ህልሟን በማስፋት አሁን ደግሞ ሌላ ህልም ሰንቃ በቀጣይ ለአህጉሯ አፍሪካ የተለያዩ ነገሮችን የማበርከት ዕቅድ ይዛለች።

"ከጊዜ ጋር ለአፍሪካ የማበረክታቸ ብዙ ነገሮች እንደሚኖሩ ተስፋ አለኝ" ስትል ምህረት አማረ በነገ ዕቅዷ ላይ ትኩረት አድርጋለች። ምን ይዛ ትመጣ ይሆን?

ኮሮና
Banner