ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ 'ቀለል ያለች ድብርት አለችብኝ' አሉ

ሚሼል ኦባማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ቀዳማዊት አመቤት ሚሼል ኦባማ 'አነስተኛ ጭንቀት' እንዳለባቸው ተናገሩ።

እመቤቷ ድብርቱ ወይም ጭንቀቱ የያዛቸው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ በዘር መድልዎና በትራምፕ አስተዳደር 'ግብዝነት' ምክንያት እንደሆነ አሳውቀዋል።

በስሜት ውጣ ውረድ መጓዝ ትልቅ ፈተና ነው ያሉት ሚሼል ኦባማ፤ መደበኛ እንቅልፍና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደተሳናቸው ተናግረዋል።

ሚሼል ኦባማ ስለጭንቀታቸው የተናገሩት በበይነ መረብ የድምፅ ኮሮጇቸው [ፖድካስት] ላይ ከአንዲት አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።

«መሰል ጊዜዎች አስደሳች እንዳልሆኑ አውቃለሁ፤ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ድብርት እንዳለብኝ አውቃለሁ» ብለዋል ቀዳማዊት እመቤቷ።

«ጭንቀቱ የሚመነጨው ቤት ውስጥ ተዘግተን በመቀመጣችን ብቻ አይደለም። እያየን ያለነው የዘር መድልዎም አስተዋፅዖ አለው። አልፎም የወቅቱ የአሜሪካ ገዥ መንግሥት በየቀኑ ግብዝ የሆኑ ነገሮችን ሲፈፅም ማየት መንፈስ ያውካል።»

ሚሼል፤ 'ጥዋት ተነስቶ አንድ ጥቁር ሰው ላይ ስለደረሰ በደል መስማት በጣም ያማል፤ ጥቁሮች ከሰው በታች ሲመዘኑ ማየት ልብ ያደማል' ሲሉ በፖድካስታቸው ላይ ተናግረዋል።

እመቤት ኦባማ፤ መሰል ጭንቀቶች ሲያጋጥሙ በተለይ በአሁኑ ወቅት ነገሮችን በክፍለ-ጊዜ መከወን አዋጭ ነው ሲሉ መክረዋል።

ሚሼል ኦባማ በመጀመሪያው ዙር የፖድካስት ስርጭታቸው ለባለቤታቸው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ቃለ-መጠይቅ አድርገው ነበር። ባራክ ኦባማ ከዶናልድ ትራምፕ በፊት አሜሪካን ለስምንት ዓመታት መርተዋል።