ኮሮናቫይረስ፡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አራት አማራጮች

የፎቶው ባለመብት, Simona Granati - Corbis
በኮቪድ19 ወረርሽኝ ምክንያት በነሐሴ ወር ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ማስፈጸም አስቸጋሪ በመሆኑ መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም ምርጫውን ማካሄድ ያስችላሉ ያላቸውን አራት አማራጮችን ማቅረቡ ተነግሯል።
እነዚህም አማራጮች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ህገ መንግስት ማሻሻል እና የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው።
ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እነዚህን አማራጮች ካቀረቡ በኋላ አንዳንድ ፖለቲከኞች 'አራቱም አማራጮች ጥሩ አይደሉም ሲሉ ተደምጠዋል'።
ቢቢሲ እነዚህ አማራጮች ጥሩ እና መጥፎ ጎናቸው ምንድነው ሲል በኔዘርላንድስ አገር የዲሞክራሲ እና የአስተዳደር አማካሪ የሆኑትን ዶ/ር አደም ካሴን አበባን እና በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሺንግተን ኤንድ ሊ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሔኖክ ገቢሳ ጠይቋል።
1ኛ አማራጭ፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን
ዶ/ር አደም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን ማለት በቀላል ቋንቋ የምክር ቤቱ አባላት የሥራ ጊዜ እንዲያበቃ ማድረግ እና መንግሥት ግን የዕለት ተዕለት ሥራውን እያከናወነ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ።
"የምክር ቤቱ አባላት ይበተኑ እንጂ የመንግሥት ካቢኔ ግን ይቀጥላል" ይላሉ።
በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 60 ጠቅላይ ሚንስትሩ የምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ማድረግ እንደሚችሉ ያስታውሳሉ።
ዶ/ር አደም መንግሥት ምርጫ ለማስፈጸም አማራጭ ይሆናሉ ብሎ ካቀረባቸው አመራጮች መካከል ይህ የተሻለው አማራጭ ይሆናል ብዬ አላስብም ብለዋል።
ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።
የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከበተኑ በኋላ የሚኖራቸው መንግሥት 'ደካማ' የሚባል ይሆናል።
በአንቀጽ 60/5 መሠረት ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ አገሪቱን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የመንግስትን የዕለት ተዕለት ሥራ ከማከናወን እና ምርጫን ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ህጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም።
"ለምሳሌ ኮቪድ-19 የሚያመጣው ከባድ የሆነ ፈተና አለ። ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ጫና አገሪቱን ሊያወጣ የሚችል አዳዲስ ደንብ እና ድንጋጌዎች መውጣት አለባቸው። መንግሥት ግን ይህን ማድረግ አይችልም። የውጪ ግነኙነታችንንም ብንመለከት ከግብጽ እና ሱዳን ብዙ ጉዳዮች አሉብን። አቅም የሌለው መንግሥት ለውጪ አገር ድርድሮችም የማይመች ነው የሚሆነው" ይላሉ ዶ/ር አደም።
ይህ ምክር ቤቱን የመበተን አማራጭ ትክክል ላለመሆኑ ሁለተኛ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፤ "ይህ እንደ አማራጭ ሆኖ መታየቱ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ያሳያል። ምክንያቱም ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 60 የፓርላማው እና የመንግሥትን እድሜ ከአምስት ዓመት ለማሳጠር እና ምርጫ ለማካሄድ ታስቦ የተቀመጠ እንጂ የመንግሥትን እድሜ ለማራዘም ታስቦ የተቀመጠ አይደለም" ይላሉ።
ይህ አማራጭ ደካማ መንግሥት ከመፍጠሩም በተጨማሪ አንቀጹ ይህን ለማድረግ ታስቦ የተቀመጠ ስላልሆነ ጥሩ አማራጭ ነው ብዬ አላስብም" ይላሉ ዶ/ር አደም።
በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሺንግተን ኤንድ ሊ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ሔኖክ ገቢሳ በበኩላቸው በአንቀጽ 60 መሠረት ምክር ቤቱ የሚበተነው የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ እንጂ መንግሥት የራሱን ስልጣን ለማራዘም በማሰብ አይደለም ይላሉ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መበተኑ አዋጭ አካሄድ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ገቢሳ "ምክር ቤቱ ተበተነ ማለት መንግሥት ተበተነ እንደ ማለት ነው። ከመንግሥት ከሶስቱ የመንግሥት መዋቅሮች (ኦርጋንስ ኦፍ ገቨርንመንት) ትልቅ ስልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ትልቁን የመንግሥት አካል ተበተነ ማለት ሕጎች ማውጣት አይችልም፣ ሚንስትሮችን እና የካቢኔ አባላትን ማስሾም አይችልም" ይላሉ።
2ኛ አማራጭ፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ
በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን እንዳለው ዶ/ር አደም ያስታውሳሉ።

"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ መንግሥት የሕገ-መንግሥቱን አንዳንድ አንቀጾች ሊገድብ ይችላል። ሊገደቡ ከሚችሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ገደብን ሊገድብ ይችላል" በማለት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የምርጫ ጊዜን ሊያራዝም የሚችልበትን አማራጭ አስቀምጠዋል።
የዜጎች የመምረጥ እና መመረጥ መብትን ጨምሮ የፖለቲካ መብቶች ተገድበው ባሉበት ወቅት ታዓማኒነት ያለው ምርጫ ማካሄድ እንዴት ይቻላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር አደም ሲመልሱ፤ "ዋናው ጉዳይ ምርጫ በአንድ ቀን የሚፈጸም ድርጊት ሳይሆን በረጅም ጊዜ የሚፈጸም ተግባር መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈለጊ እስከሆነ ድረስ ይሄዳል ከዛ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲቆም ምርጫ ማካሄድ ይቻላል። የግድ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምርጫው እስከሚካሄድበት ድረስ መቀጠል አያስፈልገውም" ይላሉ።
ዶ/ር አደም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ተኩኖ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ግን የምርጫው ውጤት ላይ የተዓማኒነት እና ነጻነት ጥያቄ ሊነሳበት እንደሚችል ያስረዳሉ።
3ኛ አማራጭ ሕገ-መንግሥትን ማሻሻል
መንግሥት ምርጫውን በማራዘም ምርጫ ለመካሄድ ሕገ-መንግሥትን የማሻሻል ሃሳብ ተፈጻሚ መሆን እንደማይችል ዶ/ር ሔኖክ ይናገራሉ።
"አሁን ያለው ችግር መንግሥት ያለውን የአምስት ዓመት እድሜ መጨመር እና ምርጫ ማካሄድ ይችላል የሚለው ነው። ሕገ-መንግሥት ማሻሻል ለዚህ ምላሽ አይሰጥም። ለምሳሌ መንግሥት ለተጨማሪ 6 ወራት በሥራ ይቀጥል ተብሎ በሕግ-መንግሥቱ ላይ ማካተት አይቻልም። አንድ ግዜ በሕግ የሚካተት ነገር ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ነው። "
ለዶ/ር ሔኖክ፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሁሉንም ይሁንታ ማግኘት አይችልም። ሁሉም በሕገ-መንግሥቱ ላይ የራሱ ፍላጎት አለው። ለምሳሌ አንቀጽ 39፣ የብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት፣ እንዲነሳ የሚፈልግ ይኖራል። ሌላው እንዲቆይ የሚፈልግ ይኖራል። በዚህም ግጭት ሊከሰት ይችላል። የማያልቅ እልቂትም ሊያከትል ይችላል።
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ በሚመለከተው አካል በበቂ ሁኔታ የሚደገፍ ከሆነ ሕገ-መንግሥቱ ሊሻሻል የሚችልበት አግባብ አለ።
"የዚህ አማራጭ መልካም ጎን ግልጽ መልስ ይሰጣል ግን ጥያቄው መፍትሄ ይሰጣል ወይ የሚለው ነው" ይላሉ ዶ/ር አደም። ሃሳባቸውን ሲያብራሩ "ሕገ-መንግሥቱ ይሻሻል ከተባለ በምን መልኩ ነው ሊሻሻል የሚችለው የሚለው ላይ መግባባት ላይ መደረስ አለበት" ይላሉ።
ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ላይ ህዝቡን ጨምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ማወያየት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ጊዜ ይውስዳል ባይ ናቸው ዶ/ር አደም።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ባለበት ወቅት ለመንግሥት ፓርቲዎች እና ህዝቡን በአንድ ላይ ሰብስቦ ማወያየት ቀላል እንደማይሆን ዶ/ር አደም ይናገራሉ።
ዶ/ር አደም ጨምረውም "ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል መንግሥት በር ከከፈተ በርካቶች እንዲቀየር የሚፈልጉትን ነገር ይዘው ወደፊት ይመጣሉ" ይላሉ፤ ከዚህ ቀደም ድርጅቶች እና ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የሕግ መንግሥቱ አንቀጾች ሊሻሻሉ ይገባቸዋል በማለት ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን በማስታወስ።
መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም፤ ምርጫ ለማካሄድ ይህን አማራጭ ለመተግበር ቢፈልግ የትኛውን የሕግ-መንግሥት አንቀጽ ሊያሻሽል ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በሕገ መንግሥቱ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ነው የሚለውን ክፍል ምክንያት እና በየትኛው አካል መቀየር እንዳስፈለገው በመጥቅስ እንደሚሻሻል ያስረዳሉ።
4ኛ አማራጭ የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ
የሕገ- መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ማለት ምን ማለት ነው? መንግሥት የሕገ-መንግስት ትርጓሜ በመጠየቅ ምርጫን ሊያራዝም የሚችለው እንዴት ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር አደም ሲመልሱ፤ "የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ ማለት ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ሲነሱ፤ ጥያቄዎችን የመፍታት ስልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የሚረዳው ደግሞ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ የሚባል አለ። 'ዜጎች የመምረጥ እና መመረጥ መብት አላቸው፤ ሕገ-መንግሥቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ነው ብሎ ይገድባል። ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አልቻልንም ምን ማድረግ አለብን' ብሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ይጠይቃል። የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ማለት ይህ ነው" ይላሉ።
ዶ/ር አደም እንደሚሉት ከሆነ ግን የአምስት ዓመት ገደቡ በፌዴሬሽን ምርክር ቤት ላይም ይሰራል። ይህ ማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ የሚጠየቀው በራሱ ጉዳይ ላይ ነው።
ዶ/ር አደም መንግሥት ካቀረባቸው አራት መፍትሄዎች መካከል "ይሄ የተሻለ ነው" ብሎ መደምደም አስቸጋሪ እንደሆነ በመጠቆም፤ "የፖለቲካ ውሳኔ የቅቡልነት ጉዳይ ነው። ፖለቲካ ፓርቲዎች እና መንግሥት የሚስማሙበት ከሆነ የትኛውም አማራጭ ተግባር ላይ ሊውል ይችላል" ሲሉ ይደመድማሉ።
ዶ/ር ሔኖክ መፍትሄ ነው ብለው የሚያስቀምጡት መንግሥት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች እንድላይ በመምጣት ሕገ-መንግሥቱ ሳይሸራረፍ ፓርቲዎች መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ ማስተዳደር እንዲችል የሚፈቅድ ዲክላሬሽን መስጠት አለባቸው የሚል ነው።
ታዲይ መንግሥት በዚህ ወቅት በህገ-መንግሥቱ የተዘረዘሩትን ግዴታዎቹን እየተወጣ መሆን ይኖርበታል ይላሉ።















