ምርጫ ቦርድ የተራዘመ ቀን ቆርጦ እንዳላቀረበ አሳወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Election Board
ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ ምርጫው በተያዘበት ቀን ነሐሴ 23፣ 2012 ማካሄድ እንደማይችል ያሳወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ለተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቅ እንጂ የተራዘመ ቀን ቆርጦ እንዳላቀረበ አስታውቋል።
ቦርዱ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደመሆኑ መጠን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ተይዘው የነበሩ ተግባራት ማከናወን እንደማይችል ጠቅሶ ወሳኔውን ለምክር ቤቱ ማሳወቁን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
በዚህም መሰረት በጊዜ ሰሌዳው ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራት እንዲቆሙ፣ የወረርሽኙ ስጋት ሲወገድ እንደገና ተገምግሞ እንቅስቃሴ እንዲያስጀምር የሚሉ ውሳኔዎች ማስተላለፉንም ለምክር ቤቱ ሪፖርት አድርጓል።
ቦርዱ በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ችግሩን ለተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረብ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ከማድረግ ውጨ ከስልጣኑ ውጪ የሰራው ወይም ስልጣኑ ኖሮት ሳይወጣ የቀረው ሃላፊነት የለምም ብሏል።
በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት በስራ ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ማድረጉን ጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ላይ ሲደረስ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁለት ዙር ውይይት መደረጉን ጠቅሶ በመግባባትም ተጠናቋል ብሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹም የወረርሽኙ አሳሳቢነት በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አይነት ላለ አገር ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ጠቅሰው ከተለያዩ የመንግሥት አካላትም ጋር በመመካከር እንዲሰራ ጠይቀዋል።













