ኮሮና ቫይረስ፡ "ከቫይረሱ በላይ የሚያስጨንቀን ረሃብ ነው?" የናይጄሪያዋ ጉሊት ቸርቻሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮና ቫይረስ መዛመትን በመፍራት ብዙ አገራት የከተሞቻቸውን እንቅስቃሴ የመገደብ እርምጃን እየወሰዱ ሲሆን ናይጄሪያም ዋና ዋና ከተሞቿ ለሁለት ሳምንታት እንዲዘጉ ወስናለች።
ሃያ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ናይጄሪያውያን እንቅስቃሴያቸው ተገድቧል። በተለይም በተጨናነቁ መንደሮች ለሚኖሩት ሁኔታው ዱብ እዳ ነው የሆነባቸው፤ የማይወጡት አዘቅት፤ እንደ ሰማይ ከባድ ሆኖባቸዋል።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ ንዱካ ኦሪጅንሞ ከናይጄሪያዋ ንግድ ማዕከል ሌጎስ የተወሰኑትን አናግሯል።
"ይሄን የምትሉትን ለእጅ መታጠቢያ የሆነውን ውሃ ከየት ነው የምናገኘው" በማለት የ36 ዓመቷ ዴቢ ኦጉንሶላ ትጠይቃለች።
የንግድ ማዕከል የሆነችውን ሌጎስ፣ አጎራባቿን ኦጉን እንዲሁም ዋና መዲናዋን አቡጃን ለሁለት ሳምንታት ያህል የመዝጋት ውሳኔ የተላለፈው በትናንትናው ዕለት ሲሆን፤ የአገሪቱም ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የቫይረሱን መዛመት ለመከላከል ብቸኛው አማራጭ ይሄ ነው ካሉ በኋላ "ይህ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው" ብለዋል።
ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ እንደ ዴቢ አጉንሶላ ላሉ ሰዎች ቤት ውስጥ መቀመጥ ፈታኝ ነው። እሷም ሆነ ቤተሰቦቿ በአንድ ቤት ውስጥ ሆነው ተጨናንቀው ነው የሚኖሩት፤ በተለምዶም ቤቶቻቸው ካላቸው መጠጋጋት የተነሳ 'ፊት ለፊት' የሚል ቅፅል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል።
የቢቢሲ ጋዜጠኛም በቦታው በተገችበት ወቅት የመብራት አገልግሎት ያልነበረ ሲሆን በቤቱ ውስጥ ጭላንጭል ብርሃን ይገባል። በአካባቢው የሚኖሩ 20 ቤተሰቦችም የሚጋሩት ሁለት መፀዳጃ ቤትና መታጠቢያ ቤት አላቸው።
"የምንፈራው ረሃብን ነው፤ ቫይረሱን አይደለም"
ዴቢ በምትኖርበት አላፔሬ የውሃ መስመርም ሆነ ውሃ ባለመኖሩ በአቅራቢያዋ ካለ አምሳ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የተሰበረ የህዝብ ቧምቧ ሄዳ ትቀዳለች።
"ከኔ በላይ የምጨነቀው ለልጆቼ ነው" ትላለች።
ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ቢሆንም አራቱም ልጆቿ እንቅልፍ ወስዷቸዋል።
"ወጥቼ አትክልትና ፍራፍሬ መንገድ ላይ ካልሸጥኩ ልጆቼ ምን ይበላሉ? እንዴትስ ይተርፋሉ" ትላለች ጉሊት በመቸርቸር የምትተዳደረው ዴቢ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለቤቷ በደቡብ ናይጄሪያ በምትገኘው ዋሪ የነዳጅ ማውጫ ውስጥ ተቀጥሮ ነው የሚሰራው፤ ቤቱም የሚመጣው በየወሩ ነው። ሆኖም በአሁኑ ወር ላታየው ትችላለች፤ ናይጄሪያ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙትን ሪቨርስ፣ ዴልታ፣ ካኖ፣ ባዬልሳ ድንበር ከተሞች መዝጋቷ፤ ከአንድ ግዛት ወደ አንድ ግዛት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲገደብ አድርጎታል።
የከተሞች መዘጋት ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ባለቤቷን የምታይበትን ጊዜ ሩቅ ያደርገዋል።
"የሚያስጨንቀኝ ረሃብ ነው፤ ቫይረሱ አይደለም። ቫይረሱ ህፃናትን እንደማይገድል ሰምቻለሁ" ትላለች ኦጉንሶላ ።
ምንም እንኳን ቫይረሱ ክፉኛ የሚያጠቃውም ሆነ የሚገድለው በዕድሜ ከፍ ያሉትን እንዲሁም ተደራራቢ የጤና እክል ያላቸውን ቢሆንም ዴቢ እንደምትለው ሳይሆን ህፃናትም በቫይረሱ እየሞቱ ነው፤ ቫይረሱንም ከሰው ወደ ሰው ያስተላልፋሉ።
ቤሳ ቤስቲን በሌለበት ሁኔታ
ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የዴቢ ብቻ አይደለም፤ የጎረቤቶቿ እንዲሁም ድንበር፣ ወንዝ፣ ባህልን ተሻግሮ በድህነት የሚኖሩባት የዓለም ሁኔታ ነው። የዴቢ ጎረቤት ተለቅ ያለ በረንዳ ያላቸው ሲሆን ሁለት በእድሜ ገፋ ያሉ ሴቶች ቁጭ ብለው ያወራሉ።
በእድሜ ተለቅ ያሉ ቤተሰቦች እንደ ልጆች ጠባቂ ሆነው ከልጆቻቸው እንዲሁም ከዘመዶች ጋር መኖር የከተሜው እውነታ ነው።
በዚህም ሁኔታ ቫይረሱ ቢዛመት በእድሜ ለገፉት ከፍተኛ ስጋት ነው።
"አሁንም ቢሆን ሰብሰብ ብለው ቤት ይቀመጣሉ። አንድ ሰው በቫይረሱ ቢያዝ በአካባቢው ያሉ ሰዎች የመያዛቸው እንዲሁም የመዛመቱ ሁኔታ በጣም ከፍተኛ ነው" ይላሉ የጤና ባለሙያው ዶ/ር ኦየዋሌ ኦዱባንጆ።
በጣልያንም የአኗኗር ሁኔታቸው ለቫይረሱ መዛመት ምክንያት ነው። አያቶች፣ አጎት፣ አክስት፣ አባት፣ እናት፣ ልጆች፤ የተለያየ ትውልድ ተሰባስበው ይኖሩባት የነበረችው ጣልያን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ህይወት አጥታለች።
ናይጄሪያም የሌሎች አገሮችን ፈር በመከተል እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ሲሆን፤ የግሉም ይሁን የመንግሥት ሰራተኞች ከቤት እንዲሰሩ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
መብራት በሚቆራረጥበት እንዲሁም ደካማ ኢንተርኔት ባለበት ሁኔታ ከቤት ሆኖ ሥራ ይሰራል ማለት አስቸጋሪ ነው።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ከተሞች መዘጋታቸውን ባወጁ ማግስት በትልልቅ መደብሮች ላይ ምግብ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ቁሶችን ለመሸመት ተሰልፈውም ታይተዋል።
ነገር ግን ይሄ የብዙ ናይጄሪውያን እውነታ አይደለም። ከእጅ ወደ አፍ ለሆነው ናይጄሪያዊ፣ ቤሳ ቤስቲን ለሌለው ናይጄሪያዊ የነገን ምግብ ማከማቸት አይደለም ዛሬን በልቶ ማደር ቅንጦት ነው።
ብዙ ናይጄሪያውን የዚህ ወር ደመወዝ እየጠበቁ ከመሆናቸውም አንፃር የኑሮ ሁኔታቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶታል።
ይህንን ሸክም ለማቃለል በሚል ፕሬዚዳነት ሙሃማዱ ቡሃሪ የደሃ ደሃ ተብለው ለተለዩ ሰራተኞች 420 ብር ቅድሚያ ደመወዝ እንዲከፈላቸው ቢወስኑም ኢ-መደበኛ በሆነ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሚሊዮኖች ናይጄሪያውያን ከአርዳታው ውጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል በማለትም እየተተቹ ነው።
"የሚሸምተውም ሆነ የሚያከማቸው ገንዘብ ያለው ነው። ገንዘብ ከሌለ ምን ማድረግ ይቻላል?" ይላል ከአንደኛው ትልቅ መደብር ውጭ የቆመ የታክሲ አሽከርካሪ።
ሌላኛው ፍራቻ ደግሞ በከተሞች ያሉ ችግሮች ከተባባሱና ከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚያጋጥም ከሆነ ብዙዎች ምግብ ለማግኘት ገጠር ወደሚገኙ ዘመዶቻቸው ለመሰደድ ይገደዳሉ።
ይህም ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የእድሜ ባለፀጎች ለቫይረሱ ያጋልጣል፤ በተለይም የጤና አገልግሎት ደካማ በሆነባቸው በነዚህ ስፍራዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮሮናቫይረስ የተያዘው የመጀመሪያው ጣልያናዊ ሲገኝ የናይጄሪያ ባለስልጣናት ግለሰቡን ለይቶ ማቆያ ውስጥ በማስገባት፤ ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን እንዲሁም ንክኪ ያላቸውን ክትትል በማድረግ ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ምስጋና ተችሯቸው ነበር።
ነገር ግን አሁን ቫይረሱ እንዳይዛመት ያደረገችው ጥረት እንዲሁም ወረርሸኙን ለመቆጣጠር ያላት የጤና ሥርዓት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
"ይህንን ጊዜ እናልፈዋለን"
አገሪቷ ያሏት መመርመሪያዎች ጥቂት ቢሆኑም ምልክቱ ያልታየባቸው የመንግሥት ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች መመርመራቸው የፍትሃዊነት ጥያቄን አጭሯል።
ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ስልጣን ሲረከቡ ለህክምና የሚደረጉ ማንኛውም የውጭ ጉዞዎችን እንደሚያስቀሩ ቃል ቢገቡም እሳቸውም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናት ለህክምና የሚያደርጉትን የውጭ ጉዞ አላቆሙም ነበር። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማግስት ግን ይህ የሚሆን አይደለም።
ሌጎስም ሆነ ሌሎች ከተሞች ስብሰባዎችንም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ቢያግዱም፤ ፓስተሮችን ጨምሮ ብዙዎች አካላዊ ርቀት መጠበቅ የሚለውን እየጣሱት ይገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አላፔሬ በሚገኘውና በተጨናነቀው የአውቶብስ መናኸሪያ ጉሊት ቸርቻሪዎች፣ እንዲሁም ጌጣጌጥና ልብሶችን መንገድ ላይ የሚሸጡ ግለሰቦች መሸጫ ቦታ ይፈልጋሉ። ከቫይረሱ በላይ የእለት ጉርሳቸው ያስጨንቃቸዋል።
"ሁሉም ሞት ሞት ነው" ትላለች በሁለት አውቶብሶች እየተመላለሰች በትሪዋ ላይ አሳ እየሸጠች የነበረች ሴት።
"ቤቴ ብቀመጥ በረሃብ እሞታለሁ፤ እዚህ መጥቼ የዕለት ጉርሴን ለማግኘት ብሞክር በቫይረሱ እንደምሞት እየነገራችሁኝ ነው"
"በህይወታችን ብዙ ፈተና አይተናል፤ ያላየነው ነገር የለም። አሁንም አለን፤ ነገን እናያለን፤ ይህንንም ጊዜ እናልፈዋለን"ብላለች።













