ኮሮናቫይረስ፡ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት ኢትዮጵያዊያን ሦስቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው

የህክምና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሦስት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው አጠቃላይ ቁጥሩ አስራ ዘጠኝ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዛሬ ዕሁድ አስታወቀ።

በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል ሁለቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የ14 እና የ48 ዓመት እድሜ ያለቸው የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

ከእነዚህ ሁለት ታማሚዎች በተጨማሪም ባለፈው አርብ በሽታው እንደተገኘባቸው የተገለጸው የ61 ዓመት ግለሰብም የዚሁ ቤተሰብ አባል እንደሆኑ ቢቢሲ ማረጋገጥ ተችሏል።

ባለፈው ሳምንት እንደተገለጸው የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የ61 ዓመቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ግለሰብ ወደ ውጪ አገር የተደረገ የጉዞ ታሪክ ያልነበራቸው ቢሆንም ከውጭ አገር ዜጋ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ግለሰቡ በበሽታው ሊያዙ መቻላቸውንና ዛሬ መያዛቸው ይፋ የተደረጉት ሁለቱ የግለሰቡ የቤተሰብ አባላት ምናልባትም ቫይረሱ ከግለሰቡ ሳይተላለፍባቸው እንዳልቀረ ተገምቷል።

ሁለቱ ሰዎች የበሽታው ምልክት ባያሳዩም ቀደም ሲል በቫይረሱ ከተያዘ ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ ስለነበራቸው በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ቆይተው ትናንት በመጋቢት 19 በተደረገላቸው የላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

አዲስ በበሽታው መያዛቸው ዛሬ ከታወቁት ሦስት ሰዎች መካከል አንደኛዋ የ26 ዓመት ኢትዮጵያዊት ስትሆን መጋቢት 8/2012 ዓ.ም ወደ ቤልጅየም ብራስል እንዲሁም መጋቢት 10/2012 ዓ.ም ደግሞ ወደ ካሜሮን ተጉዛ እንደነበር ታውቋል።

ግለሰቧ የበሽታው ምልክት ስለታየባት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ ቅዳሜ መጋቢት 19/2012 ዓ.ም በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጧል።

እስካሁን በሚመለከታቸው አካላት በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ህሙማን መካከል ኢትዮጵያዊያን 12፣ ጃፓናዊያን 4፣ አንዲት እንግሊዛዊት፣ አንድ ኦስትሪያዊና አንድ ሞሪሸሳዊ ናቸው።

ከአስራ ሁለቱ የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንድ አራተኛው የሚሆኑት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ተመርምረው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል ሁለቱ ጃፓናዊያን ወደ አገራቸው የሄዱ ሲሆን አንደኛው ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ማገገሙ ተነግሯል።

ምንም እንኳን በሽታው እንደተገኘባቸው ዛሬ ከተገለጹት ሰዎች ጋር የታማሚዎቹ አጠቃላይ ቁጥር 19 ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 16 ነው።

ኮሮና