ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ ቻይና በምርጫው እንድሸነፍ ትፈልጋለች አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ቻይና በቀጣዩ ምርጫ እንድሸነፍ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም” አሉ።
ትራምፕ ባለፉት ሳምንታት ቻይና ለኮሮናቫይረስ ስርጭት ተጠያቂ እያደረጉ ነበር። አሁን ደግሞ በምርጫው እንድሸነፍ ትፈልጋለች ሲሉ ከስሰዋል።
ዋይት ሁውስ ውስጥ ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ቻይና በወረርሽኙ ሳቢያ ከአሜሪካ “ብዙ ነገር ደርሶባታል” ብለዋል።
ቻይና ስለበሽታው ለዓለም ሕዝብ ቀደም ብላ ማስታወቅ ነበረባት ሲሉም ተችተዋል። በእርግጥ በርካቶች ፕሬዘዳንቱም በሽታውን ለመቆጣጠር የወሰዱት እርምጃ ዘግይቷል ሲሉ ይደመጣሉ።
ወረርሽኙ የአሜሪካን ምጣኔ ሀብት አላሽቆታል። ፕሬዘዳንቱ ለቀጣዩ ምርጫ ቅስቀሳ ሊጠቀሙ አስበው የነበረው ደግሞ አሜሪካን በምጣኔ ሀብት የበለጸገች አገር ማድረጋቸውን ነበር።
ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ያወጁት ትራምፕ፤ ጦርነቱ ምን እንደሚያካትት ያሉት ነገር የለም።
ለሮይተርስ ግን በደፈናው “ብዙ ማድረግ የምችለው ነገር አለ” ብለዋል።
ትራምፕ እንደሚሉት ከሆነ ቻይና ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ትፈልጋለች። ጆ ባይደን ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የሚጠቁም መረጃ እንደሌላቸውም አክለዋል።
“የዚ አገር ሰዎች ብልህ ናቸው፤ አገር የመምራት ብቃት የሌለው ሰው ይመርጣሉ ብዬ አላስብም” ብለዋል።
የመራጮችን ድምጽ በሚያሳየው አሃዝ (ፖሊንግ) እንደማያምኑ የሚናገሩት ትራምፕ፤ ባለፈው ሳምንት በዋነኛ ግዛቶች ነጥብ እያጡ መሆኑን ከሰሙ በኋላ አማካሪዎቻቸውን እንደተቆጡ ተዘግቧል።
አማካሪዎቻቸው እንደ ፍሎሪዳ፣ ዊስኮንሰን፣ አሪዞና ባሉ ቁልፍ ግዛቶች ትራምፕ ያሸንፋሉ ብለው አያስቡም።
“ጆ ባይደን አያሸንፈኝም” ሲሉ ለምርጫ ቅስቀሳ አማካሪዎቻቸው መናገራቸው ተሰምቷል።
ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊያቸው ብራድ ፓርስኬልን “እከስሀለሁ” ብለውት እንደነበር ቢገለጽም፤ ዛቻውን ምን ድረስ እንደሚገፉበት አለመታወቁን ሲኤንኤን እና ዋሽንግተን ፖስት ዘግበዋል።
በሌላ በኩል ትራምፕ ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ የተላለፈው ውሳኔ ቀነ ገደቡ ካለፈ እንደማያራዝሙት ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በላይ ከዋይት ሀውስ ያልወጡት ትራምፕ በቀጣይ ሳምንት ወደ አሪዞና የመብረር እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዘዳንቱ በቀጣይ ወራት ብዙ ሺህ ሰዎች የሚታደሙት የምርጫ ቅስቀሳ እንደሚያካሂዱም ጠቁመዋል።
አሁን በዓለም ካለው የኮሮናቫይረስ ኬዝ አንድ ሦስተኛው በአሜሪካ ይገኛል። ከ60 ሺህ በላይ ሰዎችም ሞተዋል። በተጨማሪም 26 ሚሊዮን ነዋሪዎች ሥራ አጥ ሆነዋል።













