ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያ የሞባይል ባንኪንግን ዘርፍ ለአገር በቀል ኩባንያዎች ክፍት አደረገች
በባንኮችና በጥቃቅን የገንዘብ ድርጅቶች ተይዞ የነበረውን የሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ ለሌሎችም ድርጅቶችም ክፍት እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመሪያ ወሰነ።
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የጥሬ ገንዘብን በመጠቀም የሚፈጠረው ግንኙነት ለመቀነስ ኢትዮጵያ በሞባይል ባንኪንግ ያላትን ህግ በማላላት የአገር ውስጥ ባለኃብቶች እንዲሰማሩበት ክፍት አድርጋለች። ይህም ንክኪን ለመቀነስና ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ጥሬ ገንዘብ መጠቀምን ያቆማል ተብሏል።
ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመሪያ መሰረትም ፈቃድ ለማውጣት የሚፈልጉ አምሳ ሚሊዮን ብር፣ ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆን እንዲሁም 10 ባለድርሻ ያሉት አክሲዮን መሆን እንዳለባቸው አስታውቋል።
መመሪያውም ከትናንትና መጋቢት 24፣2012 ዓ.ም ጀምሮ በተግባር ላይ የዋለ ሲሆን በቀን ስምንት ሺ ብር ያህል እንዲሁም በወር 60ሺ ብር ማውጣት ይቻላል።
የሞባይል ባንኪንግ ፈቃድ ያላቸው ኩባንያዎችም ገንዘብ የማስቀመጥ፣ ብድር፣ ኢንሹራንስ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል።
በመንግሥት ይዞታ ስር ያሉ ተቋማትም የሞባይል ባንኪንግ ፈቃድ መጠየቅ እንደሚችሉም ባንኩ በመመሪያው አስቀምጧል፥
ይህ ውሳኔም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች እንዲወዳደሩ በር ይከፍትላቸዋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ግብይይት የሚፈፅሙት በጥሬ ገንዘብ ሲሆን የሞባይል ባንኪንግ እንደ ሌሎች አገራት የተለመደ አይደለም።
በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ባለስልጣናት ብዙዎች ቤታቸው እንዲቀመጡና በተጨናነቁ ስፍራዎች መገኘት እንዲቆጠቡ ምክርም ቢለግሱም ብዙዎች ወደ ባንኮች የሚያደርጉትን ጉዞ አልቀነሱም፤ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ንክኪዎችም አልቀነሱም።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከትራንስፖርት ጀምሮ የተለያዩ ክፍያዎችን የሚፈፅመው በጥሬ ገንዘብ ነው።