ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በአማራ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የትምህርት ተቋማት ለመጠለያነት ተዘጋጁ
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ለሚባሉት ለምኖ አዳሪዎች እና ጎዳና ተዳዳሪዎች ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲጠለሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአማራ ክልላዊ መንግሥት የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
የኮሮና ወረርሽኝ እየተስፋፋ ከመምጣቱ አንፃር ይህ የማህበረሰብ ክፍል ከለላ ሊሰጠው ይገባል ብሎ ያመነው ቢሮው ለዚህ የሚረዳውን ኮሚቴ ማቋቋሙንም የቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን መኳንንት በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በክልሉ በተጋላጭነት ከሰላሳ ሺህ በላይ ለምኖ አዳሪዎች እና ጎዳና ተዳዳሪዎች ተለይተዋል።
ለማህረሰቡ የሚሆን የቦታ መረጣ፣ የምግብ ዝግጅት፣ የብርድ ልብስ እና ንጽህና መጠበቂያዎች እንዲዘጋጅ መደረጉን ኃላፊው ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ሁለት ግለሰቦች የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው መረጋገጡን ተከትሎ ከዛሬ እኩለ ቀን ጀምሮ በመላው አዲስ ቅዳም፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና በባ/ዳር ከተማ ብቻ የሚተገበር ለ14 ቀናት የሚቆይ ማንኛውንም አይነት የተሽከርካሪም ሆነ የህዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኮረና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ኮማንድ ፖስት መወሰኑ ይታወሳል።
ነዋሪዎች እና በጐ አድራጊዎች ሁሉ መጠለያ ቦታ ላይ ለሚሠባሠቡ እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የእለት የምግብ እርዳታ በሚያሠባስበው ግብረ ሃይልና የበጐ ፈቃደኛ አባላት አማካኝነት እንዲደግፉም ኮማንድ ፖስቱ ትላንት አስታውቆ ነበር።
በዚህ መሠረት ከ1ሺህ 300 በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ የማስገባት ሥራ ተጀምሯል።
ከወጣቶች፣ የጤና ባለሙያዎች እና ከሌሎችም ጋር በመሆን ለሥራው እንዲሆን ጥምር ኮሚቴ መቋቋሙን የገለጹት አቶ ጥላሁን ለሥራው ሦስት ትምህርት ቤቶች መለየታቸውን አስታውቀዋል።
የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ እና ፍራሽ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ማስገባት መጀመሩን ገልጸው ዛሬ የተለዩ ሰዎችንም የማስገባቱ ስራ ይጀመራል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶቹ 103 ክፍሎች የተለዩ ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ስድስት ሰዎች እንዲቆዩ እንደሚደረግም አክለው አስረድተዋል።