በአማራ ክልል በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሰዎችን ለመለየት ክትትል እየተደረገ ነው

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በትናንትናው ዕለት ባደረገው 66 ተጨማሪ ምርመራ ሁለቱ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት ግለሰቦች በአማራ ክልል ነዋሪ መሆናቸውን አስታውቋል

ይህንንም ተከትሎ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲሁም ንክኪ ይኖራቸዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን የመለየትና የክትትል ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ገልፀዋል።

በቫይረሱ የተያዙት ግለሰቦች በአማራ ክልል ባሕር ዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውም ተገልጿል።

ግለሰቦቹ መንግሥት ያዘዘው የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ ዕለት አስቀድሞ ከዱባይ እና ከአሜሪካ የገቡ ሲሆን፤ የበሽታውን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፤ በምርመራው መሰረትም መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።

በተለይም ከአሜሪካ የመጣው ግለሰብ 'እንኳን ደህና መጣህ' በሚሉ በርካታ ሰዎች መጎብኘቱን ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ ሲጋሩት ነበር የሚለውን ቢቢሲ ጠቅሶ ለዶ/ር ፋንታ ጥያቄ ሰንዝሮላቸዋል።

በምላሻቸውም ግለሰቡ መጋቢት 12 ከአሜሪካ መጥቶ ወደ አዊ ዞን ደግሞ መጋቢት 15 መሄዱን ማረጋገጣቸውን ገልፀው፤ አቀባበል ነበር የሚለውን የዞኑ አስተዳደር ኃላፊነት ወስዶ ከጤና ባለሙያዎች ጋር እያጣራን ነው ብለዋል።

"አቀባበል ከነበረ የሚደበቅ ነገር የለውም። በሽታው በንክኪ የሚተላለፍ ስለሆነ በሽተኛውም ቤተሰቦቹን የሚደብቅ አይመስለኝም። ጉዳዩ ሌሎችን የመርዳት ነው። የተጠቁ ካሉ ጥንቃቄ አድርገው ራሳቸውን ረድተው የሚሸጋገሩበትን ለማመቻቸት ስለሆነ እንደሚስጥር ይታፈናል ብዬ አላምንም። ተደርጎ ከሆነ እነዚህ ሰዎች መረዳት አለባቸው። ሌላውን ወገናቸውን እና ቤተሰባቸውን እንዳይበክሉ የመለየት ሥራ እየሠራን ነው" ብለዋል።

ሁለቱም ታማሚዎች በአማራ ክልል የለይቶ ሕክምና መስጫ ማዕከል የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው የሚገኝ ሲሆን እስከ ትላንት ምሽት ድረስ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተጫማሪ አስረድተዋል።

በክልሉም እስከ ትላንት ድረስ 27 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን በምርመራው መሰረት ሁለቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው ሲረጋገጥ ሌሎቹ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን ዶ/ር ፋንታ አስረድተዋል።

የአለም ጤና ድርጅትም ሆነ የተለያዩ የጤና ሚኒስትሮችም ሆነ ባለሙያዎች አበክረው እንደሚናገሩት ዶ/ር ፋንታም ግለሰቦች አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም ንክኪን ማስወገድ መፍትሄ እንደሆነና በተለይም ምልክቱ ስለማይታይ ከቫይረሱ ነፃ የመሆን ማረጋገጫ አይደለም ብለዋል።

" ከቫይረሱ ነጻ ነን ለማለት በምርመራ ብቻ የምናረጋግጠው ነው" በማለት አስረድተዋል።

በተለይም 27 ሰዎች ተጠርጥረው ምርመራ መደረጉና 25 ነፃ መሆናቸውና ሁለት ሰዎች መገኘታቸው ቫይረሱ ተዛምቷል ወይም አልተዛመተም የሚለውን ሳይሆን የሚያሳየው ዶ/ር ፋንታ እንደሚሉት ቁጥሩ ተጠርጥረው ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው የታወቁትን ብቻ የሚያሳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ከማህበረሰብ ስንቱ ተጠቅቷል ስንቱ አልተጠቃም የሚለውን እንዲሁም በክልሉ ያለው ሁለት ብቻ ነው ለማለት የክልሉን ህዝብ መመርምረን ነው ያንን መናገር የምንችለው።" ብለዋል።

በቀጣዪም በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማካሄድ እየተሠራ መሆኑንም ዶ/ር ፋንታ ገልዋል "ከክልሉ ወደ ፌደራል ማዕከል ከመላክ እዚሁ ለመጀመር የሚያስችል አንድ ማሽን አግኝተን ሶፍት ዌር ኮንፊገሬሽን እየተሠራ ነው። እሱ እንዳለቀ ክልሉ እዚሁ ናሙና እየተወሰደ ውጤቱን በአጭር ከዚሁ የምንሰማበት ቀን በቅርብ ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" በማለት አስረድተዋል።

በቅርቡ ከውጭ ሃገራት የመጡ ግለሰቦች ሪፖርት እንዲያደርጉ ክልሉ ትላንት ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ምን ያህል ሰዎች ሪፖርት እንዳደረጉ ተጠይቀው እስካሁን ሪፖርቱ እንዳልደረሳቸው አስታውቀዋል።